የአሜሪካ ድምጽ (ቮይስ ኦፍ አሜሪካ – ቪኦኤ)፤ የሚተዳደረው ዩናይትድ ስቴትስ ኤጀንሲ ፎር ግሎባል ሚዲያ በተሰኘ ኤጀንሲ ነው፡፡ ኤጄንሲው ለትርፍ ያልተቋቋሙ እና የኮሚኒዝም ርዕዮተ ዓለምን ለመከላከል የተመሠረቱ የራዲዮ ጣቢያዎችን በገንዘብ የሚደግፍ መሆኑ የሚነገርለት ነው፡፡
በዚህ አግባብ የገንዘብ ድጋፍ ከሚደረግላቸው መካከል የአሜሪካ ድምጽ አንደኛው ነው፡፡ ራድዮ ፍሪ ዩሮፕ/ራድዮ ሊበርቲ እና ራድዮ ማርቲ በዚህ ምድብ ይገኛሉ፡፡ ራድዮ ፍሪ ዩሮፕ በምሥራቅ አውሮፓ፣ ማዕከላዊ እስያ፣ የምዕራብ እስያን ክፍል በሚያቅፈው ‘የካውካሰስ ቀጣና’ እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚሠራጭ ነው፡፡ ራድዮ ማርቲ ደግሞ በስፓኒሽ ቋንቋ የሚተላለፍ “የፕሮፓጋንዳ ማሽን ነው” ተብሎ የሚገለጽ ነው፡፡ ለእነዚህ ራድዮ ጣቢያዎች ገንዘብ የሚደግፈው ኤጀንሲ፤ ድጎማውን የሚቀበለው ከአሜሪካ መንግሥት ነው፡፡ ኤጀንሲው በሥሩ ከ3 ሺሕ 500 በላይ ሠራተኞችን እንዳቀፈ ይነገራል፡፡
ከጣቢያዎች መካከል በተለይ ቪኦኤ በወግ አጥባዊው ሪፐብሊካን ፓርቲ ሰዎች ትችት የሚሰነዘርበት ነው፡፡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እ.አ.አ በ2016 ሥልጣን በያዙበት ወቅት፤ የዋይት ሐውስ ሰዎች በቀጥታ ቪኦኤ “ለአሜሪካ ጥቅም እሠራለሁ ቢልም፣ አገልግሎቱ ግን ለጠላት ያደላ ነው” የሚል ነቀፌታ ሠንዝረውበታል፡፡ ትራምፕ በዳግም ምርጫ ሳይቀናቸው ቀርቶ በመሃል ዴሞክራቶች ሥልጣን ሲቆናጠጡ ትችቱ እንዲረግብ ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንቱ ዳግም ወደ ሥልጣን ሲወጡ ቀድሞ ያቄሙበት ራድዮ ላይ ትዕዛዝ አሳልፈዋል፡፡
ባለፈው ሣምንት ጁመዓ የተላለፈው የትራምፕ ትዕዛዝ የአሜሪካን ድምጽ የፌደራል በጀት የሚያነሳ ነው፡፡ ከትዕዛዙ ጋር የተነበበው የዋይት ሐውስ መግለጫ፤ ከዚህ በኋላ “ግብር ከፋዮች ለአክራሪ ፕሮፓጋንዳ ወጪ እንዳያወጡ ያደርጋል” የሚል ሠፍሮበታል፡፡ በትዕዛዙ መሠረት የሥራ ኃላፊዎች አፈፃፀማቸውን እንዲቀንሱ፤ በሕግ የሚጠየቁትን አገልግሎት እና እንቅስቃሴያቸውን ጭምር እንዲገድቡ ተጠይቀዋል፡፡ ይህ ውሳኔ ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት ለኢትዮጵያ አድማጮች ሲደርስ የቆየውን ቪኦኤ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ እና የትግርኛን አገልግሎት ሥርጭት እንዲያቆሙ የሚያስገድድ ነው፡፡
አልጀዚራ ተመልክቼዋለሁ ያለውን ኤጀንሲው የላከውን የኢሜል መልዕክት ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ለሠራተኞች በተላከው ኢሜል የሠራተኞቹ ውል ተቋርጧል፡፡ ዘገባው የተቋረጠው ውል “ሁሉንም ሠራተኞች ሊባል በሚችል መልኩ የሚያካትት” እንደሆነ ጠቅሷል፡፡ ሠራተኞቹ ከዚህ በኋላ ወደ ቢሮ እንዳይደርሱም ተነግሯቸዋል፡፡
በሩስያ ቋንቋ የሚተላለፈው የጣቢያው ባልደረባ ሚሻ ኮማዶቭስኪይ፤ እርሷን ጨምሮ ለሁሉም ባልደረቦች የኮንትራት ጊዜያቸው ማርች 31/2025 እንደሚያበቃ የሚገልጽ መልዕክት እንደደረሳት በኤክስ ገጽ አስፍራለች፡፡ ጁመዓ እለት ከተላለፈው የትራምፕ ትዕዛዝ በኋላ ጀምሮ የቪኦኤ ሥርጭት በብዙ አካባቢዎች እንዲቆም በእስያ እና መካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ አንዳንድ ራድዮኖች ደግሞ መደበኛ ሥርጭት በማቋረጥ ሙዚቃ ብቻ እያስተላለፉ ይገኛሉ፡፡
ከውሳኔው በኋላ የተናገሩት የቪኦኤ ዋና ዳይሬክተር ማይክል አብራሞዊትዝ፤ “ከ83 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የቪኦኤ ድምጽ እንዲዘጋ ተደርጓል” ብለዋል፡፡ “የአሜሪካን ታሪክ በመናገር በመላው ዓለም ዲሞክራሲን እና ነጻነትን ስናስተዋውቅ ቆይተናል” ያሉት አብራሞዊትዝ፤ በተለይ “በአምባገነን ሥርዐት ውስጥ ለሚገኙ ሕዝቦች ተገቢና ሚዛናዊ መረጃዎችን” ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የናዚ ጀርመንን ፕሮፖጋንዳ ለመቀልበስ በሚል የተቋቋመው የአሜረካ ድምጽ፤ በመላው ዓለም ከ40 በላይ ቋንቋዎች የሚሠራጭ ነው (ነበር)፡፡ በአጠቃላይ ከ354 ሚሊዮን በላይ አድማጭ እንደነበረውም ይነገራል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












