“ሙሐመድ ፈረጅ”፤ ቀድሞ ከታወቀበት የጋዜጠኝነት ሞያ ባሻገር፣ በተለይም በነሺዳ ግጥሞች ጸሐፊነት ተደጋግሞ የተጠራ ሥም ነው፡፡ ገጣሚ ሙሐመድ ፈረጅ “የሰማያት በሮች” ሲል የሠየመውን የግጥም መድበል የፊታችን ጁመዐ መስከረም 1/2019 በአዲስ አበባ፣ በግራንድ ኤሊያና ሆቴል ከጥበብ ወዳጆች ጋር ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ መነሻ ከ“ሚንበር ቲቪ”ው አሕመድ ዓብዱረሕማን ጋር ከሕይወት ዘይቤ እና ከሥነ ግጥም ሥራዎቹ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን አንስተው ተጨዋውተዋል፡፡ መልካም ንባብ፦
ትኩረቴን ከሚስበው አንድ ነገር ልጀምር…በብዙዎች ዘንድ ገጣሚ ሲባል ‘መደበኛ’ ከሚባለው የሕይወት ዘይቤ የራቀ፣ እምብዛም ለዚህ የማይጨነቅ ተደርጎ ይወሰዳል፤ ይህ የሕይወት ዘይቤ ምርጫ ለአንዳንድ ጉዳዮች (በተለይ ለማርኬቲንግ) አመቺ ላይሆን ይችላል፡፡ አንተ በተቃራኒው ከገጣሚነት ባሻገር ከፍተኛ ጥንቃቄና የሥነ ሥርዐት ደንቦችን መከተልን በሚጠይቀው በመድረክ መሪነት (MC) ትታወቃለህ፣ የተቋማት ብራንድ አምባሳደር ነህ፣ በእለት ተዕለት ሕይወትም ተመሣሣይ ዘይቤ ትከተላለህ፡፡ ይህን ተቃርኖ ማስታረቅ እንዴት ሠመረልህ?
ገጣሚ መሆን አሊያም በሌሎች የጥበባት ዘርፎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ “መደበኛ” በሚል ከምንጠራው ማኅበረሰባዊ የአኗኗር ሥርዓት “ጥቂት ፈቀቅ” ከማለት ጋር የተቆራኘና፤ ለዚህም የወል ሥምምነት የተቸረው ልማድ ሆኖ ቆይቷል። ብዙ ጊዜ በሐሳብ አገላለጽ፣ ለውሎ በሚመረጡ ሁኔታዎችና አንዳንዴም በአለባበስ ዘዬና ምርጫ ይህ ስሜት ይንጸባረቃል። ይሁን እንጂ በእኔ አመለካከት ጥበብ እና ሥነ ሥርዓት ወይም የማኅበረሰብ ወግ አይጋጩም – ይልቁንም ይደጋገፋሉ። ገጣሚነት ውስጣዊ ስሜትን፣ ምናብንና ነጻነትን የሚጠይቅ የነፍስ ሥራ ነው፡፡ የመድረክ መሪነት (MC) እና የተቋማት የብራንድ አምባሳደርነት ደግሞ በይበልጥ ውጫዊ ኃላፊነትን፣ ጊዜን ማክበርንና አንተም እንዳልከው ከፍተኛ ጥንቃቄን ይፈልጋሉ።
ለእኔ ገጣሚነቴ በቃላት ሕይወትን ከመመርመር እና የሰዎችን ስሜት ከመንካት ጋር በቀጥታ ይገናኛል፡፡ የምከተለው የሕይወት ሥርዐት ጥበብን “ባልተገደበ ነጻነቷ” ከመቀበል ይልቅ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ በመርህ መመራትን በማስቀደም የዕለት ተዕለት ሕይወቴንና የምወክላቸውን ‘ብራንዶች’ ዋጋ ሁልጊዜም በጥንቃቄ የሚያጤን እንዲሆን ሙከራ አደርጋለሁ። ስለዚህ ለእኔ ጥበብን ከመደበኛ ሕይወት ጋር አጣጥሞ መኖር በመርህ የሚመራ የሞያ እና የሕይወት ቅኝት አድርጌ ነው የምወስደው።
የነሺዳ ግጥሞች በአብዛኛው በተወሰኑ ጭብጦች ላይ (በአላህ (ሱ.ወ) ምሕረት፣ ስለ ረመዳን፣ ስለ ሥነ ምግባር፣ ስለ ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወዘተ)…ያተኩራሉ፡፡ በተደጋገሙና ሕዝብ በሚያውቃቸው ርእሶች ላይ መጻፍ በቃላትና አገላለጽ ወደተሰለቹ (Cliche) ሊወድቅ ይችላል፡፡ የዘይቤ ድግግሞሽ ሊከሰት እንደሚችልም መገመት ይቻላል፤ ለምሣሌ አንተ ስለ ረመዳን ስትጽፍ፤ “ረመዳን ዓለሜ”፣ “የሩሕ መስከረም” እና “የጨረቃ ናፍቆት” የተሰኙ ግጥሞች አሉህ፣ የምታነሳው ስለ አንድ ርእሰ ጉዳይ ነው። በዚህ መሃል ድግግሞሹን ማስወገድና የራስን አዲስ አሻራ ማሳረፍ ለአንድ ገጣሚ ምን ያህል ፈታኝ ነው?
እውነት ነው! በተወሰኑ ጭብጦች ላይ ትኩረት አድርጎ መጻፍ በርግጥም በጣም ፈታኝ ነው። በምሣሌነት ያቀረብካቸው እንደ ረመዳን፣ የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ፍቅር እና የአላህ (ሱ.ወ) ምሕረት ያሉ ርዕሶች ከሺሕ ዓመታት በላይ የተጻፈባቸው ጥልቅ ርእሰ ጉዳዮችም ናቸው። ምናልባት እዚህ ጋር ፈተናው ጭብጡ አሊያም ርእሱ ሳይሆን የዕይታ ማዕዘኑ ነው ብዬ አምናለሁ። ለምሣሌ ስለ ረመዳን ስጽፍ፤ “ረመዳን ዓለሜ”፣ “የሩሕ መስከረም” ወይም “የጨረቃ ናፍቆት” ስል እያንዳንዱ ግጥም የየራሱ የሆነ የነፍስ ሕመም፣ የምሥል እና የቃላት አዲስነት ይኖረዋል። በርግጥ ድግግሞሽን ለማስወገድ ገጣሚው ሁልጊዜ ውስጣዊ ስሜቱን ማደስ፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ማዳመጥ እና አዳዲስ የምናብ በሮችን መክፈት አለበት።
በተደጋጋሚ ስለምንሠራውና በምሣሌነት ለማስረዳትም ስለሚቀል ረመዳንን አሁንም ብንጠቅስ፤ “በጨረቃ ናፍቆት” ረመዳንን ከጨረቃ መወለድ ጋር፣ “በሥንብት እንባ” ረመዳንን ከምሕረት ጋር፣ “በእርቀ ሰማይ” ረመዳንን ከቁርኣን ጋር እንዲሁም “በሩህ መስከረም” ረመዳንን ከአብሮነት እሴት ጋር ወዘተ እንዳነሳነው ሁሉ፤ በተለየ ማዕዘን ደግሞ በ‘አርድ ፈለስጢን’ [በፍልስጤም ምድር] ጋዛ መሬት ላይ ለምትኖር አንዲት ጀግና እናት “እንኳን ለወርሐ ረመዳን አደረሰሽ” ብለን “የቁድሷ እማማ” እያልን የሠራነው መታሰቢያም አለን። በእነዚህ ሁሉ ሥራዎች ውስጥ ዐቢይ ጭብጣችን ረመዳን ቢሆንም፤ ገጣሚው የግጥሞቹን መልዕክቶችና ማዕዘን የሚበይንበት መስክ ስለሚቀያየር የግጥሙ ጣዕም የአዲስነት ለዛን እንዲጎናፀፍ ያስችለዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
ከዚሁ ጉዳይ ብዙም ሳይርቅ በነሺዳ ግጥሞች ውስጥ ገጣሚው እንደ ልቡ የመንሳፈፍ ነጻነት ላይኖረው ይችላል፤ ምክንያቱም ሃይማኖታዊ ድንበሮችን የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ ይህ ገደብ በግልህ የፈጠራ አቅምህን ይበልጥ የሚያጠናክርልህ ነው ወይስ አሳሪ?
የምናዘጋጃቸው ሥራዎች ኃይማኖትን ማዕከል እስካደረጉ ድረስ የሃይማኖቱን መሠረታዊ ማዕቀፎች ማክበርና እዚያ ቅፅር ውስጥ መቆየቱ ደግሞ ምርጫ ያለው ነገር እንዳልሆነ አምናለሁ። በአጠቃላይ እኔ ኃይማኖታዊ እና ሥነ ምግባራዊ ድንበሮችን እንደ “እስር ቤት” ሳይሆን እንደ “ወንዝ ዳርቻ” ብናያቸው የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ። ወራጅ ወንዝ ዳርቻ ከሌለው ይበታተናል፤ ኃይሉንም ያጣል። ድንበር ሲኖረው ግን መስመር ይዞ በሥርዓት መፍሰስ ይችላል። የነሺዳ ግጥሞችም ድንበር ሲበጅላቸው የሚኖራቸው ተፅዕኖ ግዙፍ ይሆናል። በበኩሌ አጥር ውስጥ ሆኖ አንድን ጭብጥ ኪናዊ ቀለም መስጠት የፈጠራ አቅምን ያስረዋል ብዬ አላምንም። ይልቁንም የበለጠ እንድጠበብ፣ ቃላትን በሒክማ (በጥበብ) እንድመርጥ እና ዓላማ ያለው ሥራ እንድሠራ ያደርገኛል የሚል እምነት ነው ያለኝ። ምናልባትም ትክክለኛ የጥበብ ሥራ የሚፈለቀቀው ወሰን በሌለው መዋተት ውስጥ ሳይሆን፤ በሚዛናዊ መርህ ውስጥ በሚገኝ “አንጻራዊ ነጻነት” ነው ብዬ አምናለሁ።
ለምርኩዝ መድረክ በጻፍካቸው በርካታ ግጥሞች ትታወቃለህ። መድረኩ እንደምናውቀው መሪ ርእስ አለው። በዚህ ሒደት ውስጥ በርእስ መታጠር የገጣሚነት ነጻነትን አይነጥቅም? ፈተናው ምንድነው? በዚህ ሰበብ ምናልባት በሥነ ጽሑፍ ዓለም ውስጥ የፈጠራ ድርቀት የሚባለው Poetic block አጋጥሞህ ያውቃል?
እውነቱን ለመናገር በርእስ መታጠር መጀመሪያ ላይ ገደብ ይመስላል። ነገር ግን በዚያው ልክ በተለየ ሁኔታ መቆየትንና የበዛ ትኩረትን ይሰጥሃል። በምሣሌነት የቀረበው መድረካችን ምርኩዝ በየዙሩ ይዞ የሚመጣው መሪ ርእስ የኅብረተሰቡን እምነትና ሕይወት መሠረት ያደረገ በመሆኑ፤ እንደ ገጣሚ ይህንን አጋጣሚ በደስታ ነው የምቀበለው። ምክንያቱም በየመድረኩ ለሚቀርቡት መሪ ርእሶች አዳዲስ ሐሳብ ላይ መቆም እንድችል ያነሳሳኛል። ፈተናው ግን የለም ማለት አይደለም። በርግጥም Poetic Block (የስንኝ ድርቀት) አጋጥሞኝ ያውቃል። በተለይ የፕሮግራሙ ቀን ሲቃረብ፣ ለመጻፍ በማይመቹ ሁኔታዎች ስቆይና ከመድረኩ የሚጠበቀውን ትልቅ ኃላፊነት ሳስብ ስንኞች እምቢ የሚሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ያን ጊዜ በዙሪያዬ ወደሚገኙ ጎበዝ ገጣሚያን ወንድሞቼ ዞር በማለት እገዛቸውን እጠይቅና ሥራው ይዘጋጃል። በዚህ ሒደት ውስጥ ምንግዜም ሥሙን የማነሳው ገጣሚ ሙሐመድ ኢድሪስ ካሣ ይጠቀሳል። ገጣሚ ሐሰን አራጋውና ሌሎች ወንድሞችና እህቶችም የጉዞው አካል ሆነው አግዘውኝ ያውቃሉ። በአጠቃላይ ፈተናው ብቅ ሲል ብዕርን አስቀምጦ ወደ ውስጥ መመልከት፣ ዱዓ ማድረግ እና የመድረኩን ግዝፈት በምናብ ማየት ከአላህ (ሱ.ወ) እገዛ ጋር ብዙ ጊዜ መንገዱን ይከፍተዋል።
ስለ ነሺዳ ግጥሞች ስንነጋገር የመድህን ተፅዕኖ ማንሳት ይኖርብናል። የቋንቋ አጠቃቀምን በተመለከተ ቀዳሚዎቹ ግጥሞች በጥልቀታቸው የሚወደሱ፣ ከዐረቢኛ የተቀየጡ፣ ዐውዳዊ ግንዛቤን የሚጠይቁና አካባቢያዊ አገላለጾችን የያዙ በርካታ ስንኞች ነበሯቸው፤ ቀላል የማይባል ተደራሲም አላቸው። በዚህም የዘመኑ ገጣሚ የቀደሙትን ቅርስ የማስጠበቅ እና የዘመኑን ተደራሲ ፍላጎትና የቋንቋ ደረጃ የማገናዘብ ኃላፊነት ውስጥ መውደቁ አይቀርም። ያንተ ሥራዎች ላይ መጠነኛም ቢሆን [ለአብነት የጨረቃ ናፍቆት ላይ] የድሮው ተፅዕኖ ያረፈበት የሚመስል ስንኝ እንሰማለን። እዚያው ላይ ያንተን የምናውቃቸውን ስንኞችም እንዲሁ እንሰማለን። በግልህ የቀድሞውና የአሁኑ ዘመን ግጥም እንዴት ሊተሳሰር ይችላል ብለህ ታስባለህ?
የቀደሙት የሀገራችን የመድህ ገጣሚያን ያላቸው የቃላት ኃብት፣ የቋንቋ ጥልቀት ‘ሸውቅ’ን (ጽኑ ናፍቆት) እና ‘ሙሐባ’ን የሚያኖሩበት ምሥል ከሳች አቅም ወደኋላ ተመልሶ ሲታይ የሚያስደምም ነው። በዚያው ልክ የዓረቢኛ ቋንቋ እና የአካባቢያዊ ዘይቤዎች ቅኝታቸውም ለዛሬው የሥነ ጽሑፍ ውርሳችን ትልቅ ኃብት እንደሆነ ይሰማኛል።
በየዘመኑ ብቅ የሚሉ ገጣሚያን ይህንን ጥልቅና ሁሉን አቀፍ ቅርስ በማቆየትና በመጠበቅ፤ በዚያው ልክ ደግሞ በጊዜያቸው የሚኖረው ተደራሲ በሚረዳው የቋንቋና የስልት ደረጃ አመዛዝኖ የማቅረብ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል። ይህ ሲደረግ የቀድሞውና የአሁኑ ዘመን የግጥም ሥራ ኅብር እንደሚኖረው አምናለሁ። ወደ እኛ ሙከራ ስንመጣ አንተ ካነሳኸው “የጨረቃ ናፍቆት” በተጨማሪ “የብሥራት ዜና” ላይ ውስን ቀዳሚ ስንኞች ላይ ወደድሮው የአገጣጠም ለዛና የዜማ ቅርፅ በተወሰነ መልኩ ለመጠጋት ሞክረናል። ይህን ስናደርግ አሠራሩ ስለሚያምር ወይም አንዳች የተለየ ስሜት ስለሚፈጥር በሚል ኪናዊ መነሻ ብቻ ሳይሆን፤ የረመዳን ምሽቶችን በአብሮነት ማድመቅ ስሩ ከቀደመው ጥልቅ ባህል የተቀዳ መሆኑንና ቅርንጫፉ ደግሞ የዛሬውን አየር የሚተነፍስ ነው የሚለውንም ስሜት ለመፍጠር በማሰብ ነው። እውነቱን ለመናገር ያደረግነው ሙከራ እጅግ የተሳካ ስለነበር ለሥራው ማማር ትልቅ ድርሻ የነበረውን ሙንሺድ ሙኣዝ ሐቢብን ማመሥገን ይኖርብኛል። “የብሥራት ዜና” ላይ የሚገኙት የመክፈቻ ስንኞችም ተመሳሳይ ይዘትና ጭብጥ አላቸው። ወንድማማችነትን፣ እርቅንና አዎንታዊ ሒስ (ነሲሓ) መስጠትን በቀደመው የአሰኛኘት ጥበብና የነዝም (ቅኝት) አወራረድ ይዘን ቀርበናል ብዬ አስባለሁ። በአጠቃላይ በእኔ አመለካከት የቀድሞውን መሠረት ሳንለቅ የዘመኑን ቅርጽና መንፈሥ የሚሸከሙ ሥራዎችን ማቅረብ ስንችል ትስስሩ እየተጠናከረ ይሄዳል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ስለ አዲሱ የግጥም መድበል ጥቂት ንገረን…አንባቢያን መጽሐፉን መቼ ያገኙታል?
ለአንባቢያን ይዤ የመጣሁት አዲሱ የግጥም መድበል “የሰማያት በሮች” ይሠኛል። መድበሉ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የሕይወት አጋጣሚዎች፣ በመንፈሣዊ ተመስጦዎች እና በማኅበራዊ ሁነቶች ውስጥ የተጻፉና የተመረጡ ስንኞቼን ሰብስቦ የያዘ የጉዞዬ ፍሬ ነው። አጠቃላይ ‘ተውበት’ን፣ እምነትን፣ ተስፋን፣ ጽናትን እና ትህትናን የሚያንፀባርቁትንና በተወሰነ ደረጃ የኑሮና የሕይወት ልምምዳችን የሚታዘቡ ሥራዎች በመምረጥ የተካተተበት ነው፡፡ በውስን ቃላት ወደተነሳበት ሐሳብ ለመድረስ የሚሞክር ሥራ ነው ልንለው እንችላለን። ከዚህ ባሻገር “በነፍስ እንጉርጉሮ” ምዕራፉ በምርኩዝ መድረክና በነሺዳ አልበም ደረጃ ለአድማጭ ቀርበው ከነበሩ ሥራዎችም የተወሰኑትን ያካተትንበት ነው።
ጊዜውን በተመለከተ በአላህ (ሱ.ወ) ፈቃድና እገዛ የመድበሉን ይፋዊ የምረቃ ሥነ ሥርዓት መስከረም 1/2019 በአዲስ አበባ ከተማ ግራንድ ኤልያና ሆቴል በይፋ በመከወን፤ መድበሉን በዕለቱ ለተገኙ ታዳሚያንና ከተለያዩ አካባቢዎች ቅድመ ኅትመት ክፍያ ለፈጸሙ አንባቢያን እናደርሳለን የሚል ዕቅድ ይዘናል። በነገራችን ላይ በተመሳሳይ ዕለት (September 11/2026) በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ Nation Capital DMV ለማስመረቅ ቅድመ ዝግጅቶች በመካሄድ ላይ ነበር። ሆኖም በአንዳንድ ሁኔታዎች አስገዳጅነት ዝግጅቱ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል። በዚህ አጋጣሚ ይህንን ሐሳብ አንግበው ኮሚቴ በማዋቀር እየተጉ የሚገኙ ወንድምና እህቶቼን እጅግ በጣም ለማመሥገን እወዳለሁ። ወቅቱ ሲደርስ የምናሳውቅ ቢሆንም በተመሳሳይ በሌሎች የአሜሪካ ግዛቶችና የአውሮፓ ከተሞችም መድረኮች ይኖራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ባህር ማዶ ለሚገኙ አንባቢዎች መድበሉን በአማዞን ማግኘት እንዲችሉ ተመቻችቷል፡፡ ስካይሊንክ ቴክኖሎጂስ በተባለ ድርጅት አማካይነት ደግሞ ሥራዎቼን ብቻ በሚያስተዋውቅ መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) ማቅረብ እንጀምራለን፡፡ ኢንሻ አላህ!
እስካሁን ግጥሞችህ በተለያየ መንገድ ለደረሷቸው ምን መልዕክት አለህ?
ጥበብ በአጠቃላይ ነፍስን የማከም፣ የመጠገንና የማለምለም ትልቅ ኃላፊነትና አደራ አለባት ብሎ እንደሚያምን አንድ አማኝ ሰው፤ ይህን ስልት በምችለው አቅም እንደ አንድ ጠንካራ የዳዕዋ መሣሪያ ለመጠቀም ስሞክር ነበር። በግሌ እስካሁን በነበረኝ የእስላማዊ ጥበባት ጉዞ በነቢያት ታሪክ የፊልም ሥራ ትርጉም፣ በ30 ጁዝ የቅዱስ ቁርኣን የአማርኛ ትርጉም ንባብ፣ መድረክ በመምራት፣ በማስታወቂያ ሞያና በነሺዳ የግጥም ሥራዎች እንደዚሁም በቴሌቪዥን፣ በራዲዮና በህትመት ውጤቶች ሚዛናዊ የሆነውን የእስልምና አስተምህሮ በተረዳሁት ልክ ለማስተጋባት ጥረት አድርጌያለሁ። ይህ ለእኔ ሥራዬ ስለሆነ የምወጣው ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የምኖርለት የህይወት ተልዕኮዬም ጭምር ነው።
አልሐምዱሊላህ! በበርካታ ወንድሞችና እህቶች አጋዥነት የተሳኩልኝ በርካታ መልካም ነገሮች እንዳሉኝ አምናለሁ። “የሰማያት በሮች” እስከዛሬ ያልመጣሁበት አዲሱ መንገዴ ነው፤ ምናልባትም ከነሺዳ ግጥሞቼ ባሻገር የምገለጥበት ሌላኛው መልኬ። በአዲሱ ሥራዬ ውስጥ የሚተላለፉት መልእክቶች ተስፋ ለቆረጡ ተስፋን የሚያለመልሙ፣ ለደከሙት ብርታትን፣ ወደ አላህ (ሱ.ወ) እና ወደ መልካም ሥነ ምግባር ለመመለስ ለፈለጉ ደግሞ የብርሃን ጥሪና መንገድ ሆነው ቢደርሷቸው እጅግ በጣም ደስ እሰኛለሁ። ከአላህ (ሱ.ወ) ጋር ይህ ይሆናል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ።
በእስካሁን ጉዞዬና በነበረኝ ምጥን አበርክቶ በቃላት መካከል የራሳችሁን ሕይወት፣ እምነትና ስሜት አግኝታችሁ ላዳመጣችሁና ፍቅራችሁን ለገለጻችሁልኝ ሁሉ ምሥጋናዬ ከልብ ነው። አዲሱ “የሰማያት በሮች” የግጥም መድበሌ በተሳካ መንገድ አንባቢያን ዘንድ እንዲደርስ የምረቃ መርሐ ግብሩን በማቀድ፣ ዝግጅቱን ለማድመቅ አጋር በመሆንና ምሽቱን ለመታደም ከፍተኛ ጉጉት ላሳያችሁኝ የልቤ ሰዎችና ተቋማት ሁሉ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ። (ሚንበር ቲቪ)












