Home ዜናና ወቅታዊ ዜና የሕዝብ በዓላት እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ

የሕዝብ በዓላት እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው መደበኛ ስብሰባው የሕዝብ በዓላትን እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አጸደቀ። በረቂቅ አዋጁ ላይ አንዳንድ የሀይማኖት ተቋማት ውይይት እንዳላደረጉና ቅሬታ እንዳላቸው ገልጸዋል ተብሏል።

ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 4/2016 የጸደቀውን አዋጅ ላለፉት ሦስት ወራት በዝርዝር ሲመለከቱ የነበሩት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማትና ስፖርት ጉዳዮች እና የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በጋራ ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ ማቅረባቸው ተገልጿል።

የምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁ ላይ ሐሳብና ጥያቄ ማቅረባቸውን የገለፀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ አንዳንድ የሃይማኖት ተቋማት በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት እንዳላደረጉና ቅሬታ እንዳላቸው ጠቁመዋል ብሏል። ሆኖም የሃይማኖት ተቋማቱን በሥም አልጠቀሰም።

በምክር ቤቱ የጤና፣ ማኅበራዊ ልማትና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ወርቀሥሙ ማሞ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ መስጠታቸው ሲገለጽ፣ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት የተወከሉ የሀይማኖት አባቶች በረቂቅ አዋጁ ላይ ስለመወያየታቸው አስረድተዋል ተብሏል።

አዲሱ አዋጅ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕዝብ በዓላት እና የበዓላትን አከባበር የሚመለከት ሲሆን፣ ክልሎች በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ሕግ አውጥተው በክልል ደረጃ የሚከበሩ አዋጆችን አከባበር መወሰን እንደሚችሉም ተገልጿል።

ምክር ቤቱ የሕዝብ በዓላት እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅን በአንድ ድምፀ ተቅቦና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here