በኢትዮጵያ የመጀመሪው ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሰጪ ዘምዘም ባንክ፤ “ዘምዘም ረሚት” የተሠኘ የዲጂታል ገንዘብ ማስተላለፊያ መተግበሪያ ይፋ አድርጓል። ባንኩ መተግበሪያውን ይፋ ያደረገው ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 26/2019 አምስተኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን እና የመተግበሪያውን ምረቃ አስመልክቶ በአዲስ አበባ ባዘጋጀው የፓናል ውይይት መድረክ ላይ ነው።
“የወለድ አልባ ባንክን የወደፊት ዕጣ ፈንታ መቅረጽ” በሚል ከኤፍ.ኤስ.ዲ ኢትዮጵያ ጋር በተዘጋጀው ፎረም ላይ የብሔራዊ ባንክ ተወካዮች፣ የዘምዘም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እና ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንዲሁም ሌሎች የፋይናንስ ዘርፉ ተዋናዮች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው፤ የሳይበር ደኅንነት ምርመራ በማለፍ በብሔራዊ ባንክ የተሰጠውን አስፈላጊ ፈቃድ ያገኘው ዘምዘም ረሚት፤ ባንኩ ከዲያስፖራው ጋር ያለውን የፋይናንስ ትስስር ለማጠናከር እና የውጭ ምንዛሬን የሚደግፍ ነው፡፡ የባንኩ ደንበኞች ተጨማሪ የአገልግሎት ክፍያ ሳይከፍሉ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲልኩ ያስችላል የተባለው መተግበሪያው፤ የሚተገበረውን የምንዛሬ ተመንና የሚደርሰውን የገንዘብ መጠን በግልጽ እንዲያውቁ ያደርጋል። በተጨማሪም ወደ ኢትዮጵያ በሚላክ እያንዳንዱ ሐዋላ ላይ ለተቀባዩ ተጨማሪ የገንዘብ ስጦታ (ሂባ) የሚያበረክት ልዩ ጥቅም ያካትታል።
የዘምዘም ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ መሊካ በድሪ እንደተናገሩት፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ አጠቃላይ ተቀማጩ 22 ቢሊዮን ብር ማድረስ ተችሏል፡፡ ጠቅላላ ሐብቱ 31 ቢሊዮን ብር የደረሰው ባንኩ፤ 17 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለፋይናንስ ማቅረቡን ገልፀዋል።
በመድረኩ ንግግር ያረጉት የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ፣ የእስላማዊ ፋይናንሱን ተጠቃሚነት ለማስፋት ጥናቶች እና ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ገልፀው የሚቀረው ወደ ተግባር መግባት መሆኑን ጠቁመዋል። የካፒታል ገበያው አዲስ ቢሆንም እስላማዊ ፋይናንስን ያካተቱ ምርቶች ለማቅረብ እየሠራ እንደሚገኝም ገልፀዋል። በቀጣይ ሱኩክን ወደ ገበያው ለማስገባት እየሠሩ እንደሆነም ጠቅሰው የሸሪዓ ሕግን የተከተሉ ኢንቨስትመንቶችን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
ይፋዊ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እስላማዊ ፋይናንስ 4.4 ትሪሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን የእስላማዊ ባንክ ድርሻ 69.3 በመቶ ነው። ሱኩክ ወደ 1 ትሪሊዮን ዶላር የደረሰ ቢሆንም በኢትዮጵያ እስካሁን አልተጀመረም። (ሚንበር ቲቪ)












