Homeዜናና ወቅታዊዜናኢትዮጵያ በዐባይ ወንዝ እና በቀይ ባሕር ላይ ያላትን ታሪካዊና ሕጋዊ ጥቅም ታስከብራለች...

ኢትዮጵያ በዐባይ ወንዝ እና በቀይ ባሕር ላይ ያላትን ታሪካዊና ሕጋዊ ጥቅም ታስከብራለች – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ኢትዮጵያ ከግዛቷ የሚነሳውን የዐባይ ወንዝ እና በቀይ ባሕር ላይ ያላትን ታሪካዊና ሕጋዊ ጥቅም እንደምታስከብር በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወጣው መግለጫ አስታውቃለች። ሚኒስቴሩ ዛሬ ሰኞ መስከረም 25/2019 ባወጣው መግለጫ፤ ቀይ ባህር ከኢትዮጵያ ጋር በመልከዓ ምድራዊም ሆነ በታሪክም የተሳሰረ የባሕር አካል መሆኑን በድጋሚ አስታውሷል፡፡

ኢትዮጵያ የዐባይ ወንዝ ዋነኛ ምንጭ መሆኗን ያስታወሰው መግለጫው፤ በቀይ ባሕር አካባቢ ያላት ታሪካዊና መልክዓ ምድራዊ ቁርኝት የማይካድ ሐቅ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡ ማንኛውም ቀጣናዊ ውይይት እነዚህን መሠረታዊ እውነታዎች ያገናዘበ ሊሆን እንደሚገባም ገልጿል፡፡

ይህ የኢትዮጵያ መግለጫ የመጣው በግብፁ ፕሬዝዳንት ዓብዱልፈታህ አል ሲሲ አስተናጋጅነት፤ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ፣ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሸይኽ መሐሙድ እና የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄነራል ዓብዱልፈታህ አል ቡርሃን የዐባይ ወንዝ እና ቀይ ባህርን የተመለከት የጋራ መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

መስከረም 24/2019 በግብፅ የተካሄደውና አራቱ ሀገራት የተሳተፉበት አራትዮሽ የምክክር ጉባኤ የጋራ መግለጫ እንደሚለው፤ በቀይ ባህር ላይ የካርጎና መርከቦች የነፃ ዝውውር መብት መከበር እንዳለበት የሚጠቅስ ነው፡፡ የቀይ ባህር አስተዳደር እና ቁጥጥር ብቸኛ ኃላፊነትና መብት ቀይ ባህር ዳርቻ ላይ ያሉ ሀገራት ብቻ እንደሆነም ያትታል፡፡ ሀገራቱ ቀይ ባሕር እና ዐባይን ጨምሮ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ተፈጻሚነት ያላቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች እንዲከበሩም ጠይቀዋል።

ይህን ተከትሎም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ለዐባይ ወንዝ አጠቃላይ የውኃ ፍሰት 85 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ እንደምታበረክት በማስታወስ፤ የዐባይ ወንዝ አጠቃቀምን እና አስተዳደርን በተመለከተ የሚደረጉ ማናቸውም ውይይቶች እነዚህን መሠረታዊ እውነታዎች መሠረት ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥቷል።

አክሎም “የፖለቲካ ድንበሮች ቢለዋወጡም፤ የኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ዳርቻ በ30 ማይልስ ያህል ብቻ የምትርቅ በመሆኗ ስለ ቀጣናው የባሕር ጉዳዮች እና የደህንነት መዋቅር የሚደረግ ማንኛውም ውይይት የኢትዮጵያን ሕጋዊ ጥቅም እና ዘላቂ ቁርኝት ያገናዘበ መሆን እንዳለበት” ጠቅሷል።

ፖለቲካዊ አሻጥሮች፣ የማስገደድ ርምጃዎች ወይም በቀጣናው አለመረጋጋት የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች እና በእጅ አዙር የሚደረግ የትኛውም የትንኮሳ ድርጊት ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ሕጋዊ ጥቅም፣ ሚና እና ኃላፊነት ሊቀንሱ እንደማይችሉት አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁንም ለሰላም እና ውይይት እና ቀጣናዊ ትብብርን ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች። መግለጫው ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን፣ የሥርዓቷን አንድነት እና መሠረታዊ ብሔራዊ ጥቅሟን ለመጠበቅ ዝግጁ እንደሆነችም በድጋሚ አረጋግጧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular