Homeዜናና ወቅታዊዜናእስልምና በ2035 በዓለም ትልቁ ሃይማኖት እንደሚሆን አዲስ ትንበያ አመለከተ

እስልምና በ2035 በዓለም ትልቁ ሃይማኖት እንደሚሆን አዲስ ትንበያ አመለከተ

በአሜሪካ የሚገኘው ታዋቂው የጥናት ተቋም ፒው ሪሰርች ሴንተር ባወጣው አዲስ የሥነ ሕዝብ ትንበያ ሪፖርት መሠረት፣ እስልምና አሁን ባለው የዕድገት ፍጥነት ከቀጠለ እ.አ.አ እስከ 2035 ድረስ የዓለም ትልቁ ሃይማኖት እንደሚሆን ይጠበቃል። ማዕከሉ ባወጣው ጥናት እስልምና እና ክርስትና ሃይማኖቶች በመጪዎቹ ዐሥርት ዓመታት የተከታዮቻቸው ቁጥር እንደሚጨምር ቢጠበቅም የሙስሊሞች ቁጥር “በፍጥነት ስለሚያድግ” አንደኛ ደረጃን ይረከባል፡፡

ጥናቱ 201 ሀገራትንና ግዛቶችን ያካተተ ሲሆን፣ ከዓለም ሕዝብ 99.98 በመቶውን የሸፈነ እንደሆነ ተጠቅሷል። ከ2020 እስከ 2070 ባሉት ዓመታት ውስጥ የሰባት የሃይማኖት ቡድኖችና አጋሮች ማለትም ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶች፣ ሂንዱዎች፣ ቡዲስቶች እና የሌሎችን የጂኦግራፊያዊ ሥርጭት እና የወደፊት ለውጦችን በጥናቱ አካቷል።

ጥናቱ እንደሚያሳየው በ2035 የዓለም የሙስሊም ሕዝብ ብዛት 2.57 ቢሊዮን ሲደርስ፣ የክርስቲያኖች ቁጥር ደግሞ 2.52 ቢሊዮን ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የዕድገቱ ዋና ምክንያት የተባለው የሙስሊሞች ከፍተኛ የወሊድ ምጣኔ ሲሆን ሙስሊም ሴቶች በአማካይ 3.1 ልጆችን እንደሚወልዱ አክሏል። እንዲሁም ክርስቲያን ሴቶች በአማካይ 2.5 ልጆችን በመውለድ በዓለም ሁለተኛውን ከፍተኛ የወሊድ ምጣኔ ይዘዋል።

በተፈጥሯዊ የሕዝብ ለውጥ ሳቢያ ሙስሊሞች እስከ 1.6 ቢሊዮን ሰዎች ሲጨምሩ፣ ክርስቲያኖች የሚጨምሩት 792 ሚሊዮን ብቻ እንደሆነ ጥናቱ አመልክቷ። በሌላ በኩል ከእስልምና የሚወጡ ሰዎች ቁጥር በጥናቱ ትንበያ መሰረት 8 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚሆኑ ሲገመት በአንጻሩ ከክርስትና የሚወጡ ሰዎች ቁጥር 105 ሚሊዮን እንደሚሆን አስቀምጧል። ይሁን እንጂ ከክርስትና የሚወጡ ሰዎች ወደ የትኛው ሃይማኖት እንደሚገቡ ያልተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ሃይማኖት አልባ ሊሆኑ የሚችሉትንም ያካተተ ነው ተብሏል።

የጥናቱ ዋና የሥነ ሕዝብ ተመራማሪ ኮንራድ ሃኬት በበኩላቸው “ጉዳዩ የልደት ብዛት ነው” በማለት ገልጸዋል። ከ2020 እስከ 2070 ድረስ ባለው የረዥም ጊዜ አዝማሚያ የዓለም አጠቃላይ ሕዝብ ብዛት በ29 በመቶ ሲያድግ፤ የሙስሊሞች ቁጥር በ80 በመቶ እንዲሁም የክርስቲያኖች ቁጥር በ30 በመቶ እንደሚጨምርም የፒው ሪሰርች ትንበያውን አስቀምጧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፒው ሪሰርች ሴንተር ትንበያዎቹ የአሁኑ የሥነ ሕዝብ አዝማሚያዎች ቢቀጥሉ የሚከሰቱ ሁኔታዎችን የሚያሳዩ እንጂ፤ ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን፣ ጦርነቶችን፣ የተፈጥሮ አደጋዎችን ወይም ድንገተኛ የሃይማኖት መነቃቃቶችን ሙሉ በሙሉ እንደማያካትቱ አሳስቧል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular