ሰኞ , محرم 9, 1446
Google search engine
Homeዜናና ወቅታዊዜናበትምህርት ተቋማት ውስጥ ከሚደረግ አለባበስ ጋር በተገናኘ አፈጻጸሙ በትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ እንዲወሰን...

በትምህርት ተቋማት ውስጥ ከሚደረግ አለባበስ ጋር በተገናኘ አፈጻጸሙ በትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ እንዲወሰን ተደረገ

በሰላም ሚኒስቴር የቀረበው የሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ በትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚኖረውን አለባበስ የተመለከተውን አፈጻጸም ትምህርት ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ እንዲወሰን አደረገ፡፡ በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተከናወነ የመጨረሻ የተባለ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ቅሬታውን አቅርቧል፡፡

በሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም የተረቀቀው አዋጅ በስድስት ክፍሎች እና በ32 አንቀጾች የተዘጋጀ ነበር፡፡ ቀዳሚውን ረቂቅ አዋጅ የተቃወመው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ “ነባር ችግሮችን ከመቅረፍ ይልቅ የሚያባብሱና ተጨማሪ ችግሮችን የሚያስከትሉ” አንዳንድ ድንጋጌዎች እንዳሉበት ጠቁሞ ነበር፡፡

ምክር ቤቱ በወቅቱ በዋና ጸሐፊው ሐጂ ሐሚድ ሙሣ በጻፈው ደብዳቤ፣ ረቂቅ አዋጁ የእስልምናን “ልዩ የአምልኮ ባሕርያት ተረድድቶ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ይልቅ አምልኮ መከልከል ላይ” ያተኮረ ነው በሚል ትችት አቅርቦበታል፡፡ የሰላም ሚኒስቴር የአዋጁን ረቂቅ ለምክር ቤቱ በጽሑፍ ሳያደርስ መቅረቱም በወቅቱ በቅሬታ የቀረበ ጉዳይ ሆኖ አልፏል፡፡

ባቀረበው ረቂቀ አዋጅ ላይ ቅሬታ የተሰማበት የሰላም ሚኒስቴር፣ ባለፈው ሳምንት ግንቦት 20/2016 የተሻሻለው ነው ያለውን ረቂቅ በማቅረብ የመጨረሻውን የግብዓት ማሰባሰብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ አካሄዷል፡፡ በዚህ የግብዓት ማሳባሰቢያ ላይ ከእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አምስት ተወካዮች መሳተፋቸውን “ሚንበር ቲቪ” ሰምቷል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙ የምክር ቤቱ ተወካዮች በዋነኛነት ቅሬታ ካቀረቡባቸው ጉዳዮች ውስጥ በአንቀጽ 15 ላይ የተጠቀሰው የአምልኮ እና አስተምህሮ አተገባበር ይገኝበታል፡፡ “ሚንበር ቲቪ” የተመለከተውና ተሻሽሎ በቀረበው አዋጅ ላይ የተካተተው አንቀጽ “በመኖሪያ አካባቢዎች፣ ማጓጓዣዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የአየር መንገድ ተርሚናሎች፣ ወታደራዊ ካምፕ፣ ሕክምና ቦታዎች፣ በሕዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች” ላይ ሃይማኖታዊ ተግባራትን ማከናወን ከልክሏል፡፡ የምክር ቤቱ ተወካዮች በዚህ አንቀጽ ውስጥ በተካተቱት ዝርዝሮች ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በማሰማት አንቀጹ እንዲሰረዝ አቤቱታ ማቅረባቸው ነው የታወቀው፡፡  

በተመሳሳይ ረቂቅ አዋጁ በአንቀጽ 17 ላይ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ረቂቁ በዚህ አንቀጽ ስር “በመንግሥት ተቋም ቅጥር ግቢ ወይም ቢሮ ውስጥ በመሆን ሃይማኖታዊ ትምህርትን ማስተማር ወይም በቡድን የአምልኮ ተግባር ማከናወን” የተከለከለ መሆኑን አስፍሯል፡፡

በሌላ በኩል በአዋጁ አንቀጽ 19 የተቀመጠው ከዚህ ቀደም በተለይ በሙስሊም ተማሪዎች ቅሬታ ሲቀርብበት የቆየው “መደበኛ ትምህርት እና ሃይማኖታዊ ተግባራት”ን የተመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ የሰላም ሚኒስቴር መጀመሪያ ባዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ በዚህ አንቀጽ ስር በማንኛውም የትምህርት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ ሃይማኖታዊ ትምህርትን ማስተማር ውም በቡድን ማምለክን ይከለክል ነበር፡፡ ሃይማኖታዊ አለባበስን በተመለከተም “ማንነትን ለመለየት በሚያስችል መልኩ” ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚገባ ጠቅሶ ነበር፡፡ ሆኖም በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ላይ በትምህርት ተቋም ቅጥር ግቢ የሚደረገው ሃይማኖታዊ ተግባር “የመንግሥትና ሃይማኖትን መለያየት መርህን እና የሃይማኖት ነጻነትን በጠበቀ መልኩ መከናወን አለበት” በሚል የተካ ቢሆንም የዚህ አንቀጽ ዝርዝር አፈጻጸም የተተወው ትምህርት ሚኒስቴር ለሚያወጣው መመርያ ነው፡፡

“ሚንበር ቲቪ” ያናገራቸውና በግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የሕግ ክፍል ባልደረባ የሆኑት የሕግ ባለሞያው አቶ ሳቢር ይርጉ፣ አዋጁ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ከመመራቱ በፊት ለውይይት መቅረቡን በአዎንታዊ ቢጠቅሱም አዋጁ አሻሚ ጉዳዮች እንዳሉበት ገልጸዋል፡፡

አቶ ሳቢር በረቂቅ አዋጁ ላይ በርካታ ጉዳዮች በቀጣይ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ለሚወጡ መመርያዎች መተዉ ቀድሞ የነበረውን ሙስሊሞች ቅሬታ ሲያቀርቡበት የቆዩትን አሠራር የሚደግም እንዳይሆን ያላቸውን ሥጋትም አጋርተዋል፡፡ የሕግ ባለሞያው በዚህ አዋጅ ላይ የተካተቱ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚወጡ መመሪያዎች የግለሰብ ፍላጎቶችን ማራመጃ እንደነበሩም በማስታወስ ጉዳዩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደው መድረክ ላይ በቅሬታ መነሳቱንም አስረድተዋል፡፡  

የሰላም ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት የመጨረሻ ያለውን ግብዓት በሰበሰበበት መድረክ የተነሱ ሐሳቦችን በግብዓትነት በመውሰድ በቀጣይ ለሚመለከተው አካል የሚቀርበውን ረቂቅ አዋጅ እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለበርካታ ዓመታት ሙስሊም ተማሪዎች ከአለባበስ እና ሰላት ጋር በተገናኘ በሚደረጉ ክልከላዎች ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ ጫና ማሳደሩ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ጉዳዩ በተማሪዎች፣ በማኅበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የማስተካከያ ርምጃ እንዲወሰድ ሲጠየቅበት የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Google search engine

Most Popular

Recent Comments