Homeዜናና ወቅታዊዜናከስምንት ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያን ሑጃጆች ሳዑዲ ዐረቢያ መድረሳቸው ታወቀ

ከስምንት ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያን ሑጃጆች ሳዑዲ ዐረቢያ መድረሳቸው ታወቀ

የኢትየጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እስከ ዛሬው እለት ድረስ 8 ሺሕ 190 ምዕመናንን ወደ ሳዐዲ ዐረቢያ መላኩን አስታወቀ፡፡ እንግዶቹን የምታስተናግደው ሳዑዲ ዐረቢያ፣ ወደ ሀገሯ የገቡ ምዕመናን ቁጥር አንድ ሚሊዮን እየደረሰ መሆኑን ገልጻለች፡፡

ለዘንድሮው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ኢትዮጵያ 12 ሺሕ ምዕመናንን እንደምትልክ ይታወቃል። ከምዕመናኑ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ተጓዦች ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ያመሩት ግንቦት 13/2016 ነበር።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተከናወነው በረራ 8 ሺሕ 190 ኢትዮጵያውያን ምዕመናን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ መጓዛቸውን በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ እና የሐጅ ኮሚቴ የሲስተም ተጠሪ አቶ አንዋር ሙስጠፋ ለሚንበር ቲቪ ገልጸዋል።

ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 27/2016 ሌሊት በረራዎች እንደሚከናወኑ የጠቆሙት አቶ አንዋር፣ በነዚህ በረራዎች ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን ቁጥር ወደ ዘጠኝ ሺሕ እንደሚጠጋ አስረድተዋል። ምክር ቤቱ ሑጃጆቹን የሚልከው እስከ ሰኔ 2/2016 ድረስ መሆኑንም ከዚህ ቀደም አስታውቋል፡፡

ከግንቦት 1 አንስቶ ከመላው ዓለም ምዕመናንን እየተቀበለች የምትገኘው ሳዑዲ ዐረቢያ፣ እስካሁን ድረስ የደረሱት ምዕመናን ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን እየተጠጋ መሆኑን አስታውቃለች። የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ይፋ ያደረጉት እስከ እሑድ የመጨረሻ ሰዓት ድረስ ያለውን መረጃ ነው።

ባለሥልጣናቱ ይፋ ባደረጉት አሐዝ መሠረት ከተለያዩ ሀገራት ሳዑዲ የደረሱ ምዕመናን ቁጥር 935 ሺሕ 966 ነው፡፡ በባሕር፣ በየብስ እና በአየር ወደ ሳዑዲ ከገቡት ምዕመናን ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በአየር ተሳፍረው መዲና የደረሱት ናቸው፡፡ እነዚህ ምዕመናን ቁጥራቸው 896 ሺሕ 287 መሆኑን የገለጹት የሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት፣ 37 ሺሕ 280 በየብስ እንዲሁም 2 ሺሕ 399 ምዕመናን ደግሞ በባሕር ሀገራችን ገብተዋል ብለዋል፡፡

ሳዑዲ ዐረቢያ በዘንድሮው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ከመላው ዓለም የምትቀበላቸው ምዕመናን ብዛት ከሁለት ሚሊዮን ይሻገራል ተብሎ ይጠበቃል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular