የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግል ቤት አከራይ እና ተከራይ በአዲሱ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ መሠረት ውል መፈፀም የሚጀምሩበትን ቀን ይፋ አደረገ። የከተማ አስተዳደሩ ውል ለመፈፀም የአንድ ወር ጊዜ አስቀምጧል።
የከተማ አስተዳደሩ ውል ለመፈፀም የጊዜ ሠሌዳው ያስቀመጠለት አዲሱ አዋጅ፣ በመጋቢት ወር መገባደጃ በሕዝብ ተወካዮች ምክር የፀደቀ መሆኑ ይታወቃል። በአዋጁ ድንጋጌዎች ላይ ከዚህ ቀደም የተደረገ ማንኛውም የአከራይ እና ተከራይ ስምምነት እንዲቋረጥ ካልተደረገ በስተቀር በአግባቡ መረጋገጥ እና መመዝገብ እንዳለበት ሠፍሯል።
ውሉ መመዝገብ እና መረጋገጥ ያለበት በአዲሱ አዋጅ መሠረት የሚቋቋመው ተቆጣጣሪ አካል በተሰየመ በ30 ቀናት ውስጥ እንደሆነ የተቀመጠ ቢሆንም የውል ማረጋገጫ እና የምዝገባ ጊዜውን እንደ አስፈላጊነቱ እስከ ሦስት ወር ድረስ ሊራዝም እንደሚችልም ተደንግጓል።
በዚህ መሠረት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አዋጁን በመመሪያ በማስደገፍ ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት ማጠናቀቁን ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 27/2016 አስታውቋል። ቢሮው የግል መኖሪያ ቤት አከራይ እና ተከራይ ሰነዶቻቸውን በማሟላት ከሰኔ 1 እስከ ሰኔ 30/2016 ድረስ ውል መፈፀም እንደሚችሉ ገልጿል። የውል መፈፀሙ ሒደት ከሥራ ሰዓት ውጪ በምሽት ጭምር የሚካሄድ መሆኑንም የቢሮው ኃላፊዎች ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ እንዲሁም በክልሎች የሚቋቋም ተቆጣጣሪ አካል በሚወስነው መሠረት ተግባራዊ በሚደረገው አዋጅ፣ የቤት ኪራይ ጭማሪ ማድረግ የሚቻለው በየዓመቱ ከሰኔ 30 ጀምሮ ለአንድ ዓመት በሚጸና ተመን ነው። የተቆጣጣሪ አካሉ ጭማሪውን የሚያደርገው የሀገሪቱን ነባራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነም ተቀምጧል።












