Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችበሐጅ ሥነ ሥርዐት ወደ ቀጣይ ዓለም የተሻገሩ ምዕመናን

በሐጅ ሥነ ሥርዐት ወደ ቀጣይ ዓለም የተሻገሩ ምዕመናን

ናይጄሪያዊው ኦሎሾግቦ ኢድሪስ ለ1445 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የገቡት ከሀገራቸው ሰዎች ጋር ነበር፡፡ የ68 ዓመቱ ኢድሪስ፣ ከሀገራቸው ሲነሱ የወጠኑት ሳይሞላ አይቀሬው ገጠማቸው፡፡ ናይጄሪያዊው የአላህ እንግዳ ኢድሪስ ወደ ቀጣዩ ዓለም ተሻገሩ፡፡ የኢድሪስን ድንገተኛ ኅልፈት ይፋ ያደረጉት የናይጄሪያ የሐጅ ጉዳዮችን የሚያስፈጽሙ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት፣ የሰውየው ኅልፈት የሆነው ማዕድ ላይ በተቀመጡበት ነው፡፡ ኢድሪስ ለማዕድ የተቀመጡት ካዕባን “ዘይረው” ከተመለሱ በኋላ ነበር፡፡

የምዕራብ አፍሪካዋ ሀገር ናይጄሪያ ለሐጅ የላከችው ዜጋዋን ኅልፈት ስትሰማ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ቀደም ባለው ሳምንት ሌላ ምዕመን ወደ ቀጣዩ ዓለም ተሻግረዋል፡፡ እኒህ ምዕመን ተወከልቱ አሊኮ የሚባሉ እናት ናቸው፡፡ ከኬቢ ግዛት የተነሱት ምዕመኗ፣ መካ ውስጥ በድንገት ተዝለፍልፈው መውደቃቸው ነው የተነገረው፡፡ አሊኮም እንደ ኢድሪስ ሁሉ ሥርዐተ ቀብራቸው እዚያው ተፈጽሟል፡፡ ናይጄሪያ ባለፈው ዓመት በተከናወነው የሐጅ ሥነ ሥርዐት የ13 ዜጎቿ ሕይወት አልፏል፡፡  

በዘንድሮው የሐጅ ሥነ ሥርዐት እንደ ናይጄሪያውያኑ ሁሉ የሌሎች ሀገራት ዜጎችም በመካ ውስጥ ባሉበት ኅልፈታቸው ተሰምቷል፡፡ እስካሁን ድረስ በወጡ መረጃዎች በርካታ ዜጎች የሞቱባት ባንግላዴሽ ነች፡፡ ባንግላዴሽ 10 ዜጎቿ ለሐጅ በሄዱበት ወደ አኺራ ተሻግረዋል፡፡ ኅልፈታቸው የተሰማው ከሀገሪቱ ከተነሱ ምዕመናን ውስጥ ትንሹ ዕድሜ 48 ሲሆን ትልቁ ደግሞ 89 ነው፡፡ አስረኛው የባንግላዴሽ ዜጋ ኅልፈት ይፋ የተደረገው ትናንት ግንቦት 27/2016 ነው፡፡ ኅልፈቱ የተሰማው ምዕመን መቅሱድ አሕመድ የሚባል ነው፡፡ የባንግላዴሽ ባለሥልጣናት ስለ ምዕመናኑ የቀደመ የጤና ሁኔታ ያወጡት መረጃ ባይኖርም የሐጅ ሥነ ሥርዐቱ የሚከናወንባት ሳዑዲ ዐረቢያ የአየር ንብረት በምዕመናን ፈታኝ ሁኔታዎችን ሊፈጥር የሚችል መሆኑ ተደጋግሞ የሚነገር ነው፡፡

የሳዑዲ ዐረቢያ የሜትሮሎጂ መስሪያ ቤት ትናንት ማክሰኞ ባወጣው መረጃ፣ በተያዘው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት በሚከናወንበት ወቅት ከእኩለ ቀን በኋላ በመካ የሚጠበቀው የሙቀት መጠን ከ45 እስከ 48 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይገመታል፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ አይመን ቢን ሳሊም ጉላም ሙቀቱ እጅግ የበረታ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ጉላም በዚህ የሐጅ ወቅት ዝናብ ዝናብ የመፈጠር ዕድሉ አነስተኛ ቢሆንም በጣኢፍ አካባቢ ደመና ሊከሰት ይችላል የሚል ግምት መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

የሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ስር የሰደደ ሕመም ያለባቸው ሑጃጆች የሕክምና ሠነድ መያዝ እንዳይዘነጉም ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር፡፡ ለዓመታዊው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የሚያመሩ ምዕመን ከጤናቸው ጋር ተያይዞ የኮቪድ19ና ሌሎች ክትባቶችን መውሰድ እንደሚኖርባቸው ቀደም ብሎ ተነግሯል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular