በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ሸሪዓን መሠረት በማድረግ ለመድሕን ሰጪነት በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው “አማና ኢንሹራንስ”፤ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ያለውን የመጨረሻ ሒደት እያጠናቀቀ እንደሚገኝ አደራጆቹ ገልጸዋል፡፡
እንደ አደራጆቹ መረጃ ከሆነ፤ ኩባንያው ሥራ ለመጀመር ካደረጋቸው ዝግጅቶች መካከል ከብሔራዊ ባንክ የከፍተኛ የሥራ አመራሮችን ማጽደቅ ይገኝበታል። ለዚህም ሲባል በዓለም አቀፍ ደረጃ በተካፉል ኢንሹራንስ የረዥም ዓመታት ልምድ ያላቸው ሱዳናዊ ባለሞያ የኩባንያው ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲሠሩ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል።
አማና ኢንሹራንስ ከብሔራዊ ባንክ የሚጠበቀውን የመጨረሻ የሥራ ፈቃድ በሚቀጥሉት ከሁለት እስከ አራት ሣምንታት ውስጥ በማግኘት በበጀት ዓመቱ የመጀመርያው ሩብ ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለመግባት እቅድ ይዟል። የሂጅራ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢና ከኩባንያው አደራጆች መካከል አንደኛው የሆኑት አቶ ዓብዱሰላም ከማል ለካፒታል ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በሙሉ አቅም ወደ ገበያው ለመግባት በማዕከላዊ ባንክ የተጠየቀውን የመጨረሻው የቁጥጥር ግብረ መልስ በዚህ ሣምንት አቅርበዋል፡፡ “ያልተጠበቀ የቢሮክራሲ መዘግየት ካላጋጠመ በስተቀር” በሚቀጥሉት 10 እና 15 ቀናት ወይም ቢበዛ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ “የሥራ ፈቃዱን እናገኛለን ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል።
አማና ኢንሹራንስ ለምሥረታ ያስመዘገበው የተከፈለ ካፒታል 260.4 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ መጠን ብሔራዊ ባንክ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች ካስቀመጠው የ400 ሚሊዮን ብር አነስተኛ የካፒታል መጠን ያነሰ ነው። ሆኖም የአደራጅ ኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ አሕባቡ ዓብደላ ካፒታሉ የተሰበሰበው አዲሱ መመሪያ ከመውጣቱ በፊት ስለሆነ፤ አማና ኢንሹራንስ የካፒታል መጠኑን ለማሟላት “ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ የእፎይታ ጊዜ እንደተሰጠው” ገልጸዋል። ለዚህም ሲባል ኢንሹራንስ ኩባንያው በቀጣይ ተጨማሪ አክሲዮኖችን በመሸጥ ካፒታሉን ለማሳደግ አቅዷል ሲሉ ገልጸዋል።

ሥራ ለመጀመር የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛል የተባለው አማና ኢንሹራንስ በአሁኑ ወቅት የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር 100 ደርሰዋል፡፡ በዚህ ማዕቅፍ ውስጥ በአምራች፣ በገቢና ወጪ ንግድ እንዲሁም በችርቻሮ ዘርፍ የተሰማሩ ታዋቂ ነጋዴዎች ተካተዋል፡፡ ከባለድርሻዎቹ መካከል በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ከሚሰጡ አራት ባንኮች ውስጥ ሦስቱ ይገኙበታል። እነዚህ ባንኮች ሂጅራ፣ ራሚስ እና ሸበሌ ናቸው። አቶ ዓብዱሰላም እንዳሉት፤ ከባንኮች መካከል ሂጅራ ባንክ እና ራሚስ ባንክ የድርሻ ክፍያቸውን ሙሉ ለሙሉ አጠናቀዋል፡፡ ሌሎች ባለድርሻዎችም የሚጠበቅባቸውን ክፍያ እያጠናቀቁ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
በቴክኒካዊ ምክንያቶች በሦስቱ መሥራች የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ሊካተት ያልቻለው ዘምዘም ባንክ፣ ኩባንያው ሥራ ከጀመረ በኋላ በሁለተኛው ዙር የአክሲዮን ሽያጭ አማካኝነት የአማናን ባለቤትነት ይቀላቀላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡
አማና ኢንሹራንስ የፈራሚዎች ጉባኤ ያካሄደው የካቲት 23/2017 ነበር፡፡ የመጀመርያውን ጠቅላላ ጉባኤውንም ሥራ በጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጥራት ውሳኔ ማሳለፉ ተነግሯል፡፡ ቀሪዎች ባለአክሲዮኖችም ያለተከፈለ ዕዳቸውን እንዲያጠናቅቁና ወደ ቀጣዩ የካፒታል ማሳደግ ዕቅድ እንዲሸጋገሩ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
ብሔራዊ ባንክ፤ አዲስ ባዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በ16ኛው ክፍል ላይ ሸሪዐን መሠረት ያደረገ የኢንሹራንስ አገልግሎት ማለትም “ተካፉል”ን የተመለከቱ ጉዳዮችን አስፍሯል፡፡ የቀደመው አዋጅ የኢንሹራንሶች አስተዳደር በቦርድ ቁጥጥር ይደረግበት የነበረ ሲሆን፤ በአዲሱ አዋጅ “የልዩ የብቃት ምዘና እና የሸሪዓ ኮሚቴ” መስፈርት ተቀምጧል፡፡
አዋጁ ሲጸድቅ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ቁጥጥር ባለሥልጣን “የተካፉል፣ የተካፉል መስኮት እና የውጭ ተካፉል ኦፕሬተሮችን” የፈቃድ አሰጣጥ መስፈርቶችን በመመሪያ እንደሚወስንም ያትታል፡፡ ይህ አዋጅ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባለሥልጣኑ የተካፉል ኢንሹራንስ ከተለመደው ኢንሹራንስ “ካለው የተለየ ባሕርይና የአሠራር ዘይቤ አንጻር” ለቁጥጥርና ለፈቃድ አሰጣጥ የሚያስፈልጉ ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታዎችን በመመሪያ ያወጣል በሚል ደንግጓል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












