Homeዜናና ወቅታዊዜናበአወሊያ ት/ቤት የፒያሳ ቅርንጫፍ ውስጥ የሚማሩ 350 ተማሪዎች እጣ ፈንታ ምንድን ነው?

በአወሊያ ት/ቤት የፒያሳ ቅርንጫፍ ውስጥ የሚማሩ 350 ተማሪዎች እጣ ፈንታ ምንድን ነው?

በአዲስ አበባ በሁሉም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶቹ ከ5 ሺሕ 500 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ የሚገኘው አወሊያ ትምህርት ቤት ከ60 ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡

ከቅርጫፎቹ መካከል ፒያሳ በሚገኘው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ አጠገቡ ያለውን ቦታ ጨምሮ ከማስፋፊያው ጋር ተደምሮ በ3 ሺሕ 600 ካሬ ላይ የሚያርፍ ባለ 19 ፎቅ ሕንጻ ለመገንባት የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ፣ የዓለም ሙስሊም ሊግ ዋና ጸሐፊ ሙሐመድ ቢን ዓብዱልከሪም አል ዒሣ እና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በተገኙበት በ2016 የመሠረተ ድንጋይ ተጥሎ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ከአንድ ዓመት በኋላ “ቦታው ለልማት ይፈለጋል” ያለው የአዲስ አበባ ከንቲባ ቢሮ በአቅራቢያ ሰባራ ባቡር በመባል በሚጠራው አካባቢ ምትክ ቦታ መስጠቱ ተነግሯል፡፡ ይህን ተከትሎም ጥቅምት 27/2019 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጅ ኢብራሂም ቱፋ ጋር በጋራ በመሆን በቦታው ላይ ባለ 10 ወለል ሕንጻ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውን ጠቅላይ ምክር ቤቱ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ከፎቶግራፍ ጋር አጋርቷል፡፡

ትምህርት ቤቱን የሚያስተዳድረው አወሊያ ርዳታ እና ልማት ድርጅት፤ በርካታ ዐስርት ዓመታት ባስቆጠረው በታሪካዊው የፒያሳ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት የነበረበትን 1 ሺሕ 449 ካሬ ሜትር ይዞታ ምትክ በመንግሥት በኩል ወደ 7 ሺሕ ካሬ ሜትር ገደማ ቦታ እንደተረከበም ገልጿል። በሂደት ቀሪውን 3 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ እንደሚረከቡ የአወሊያ ርዳታ እና ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰዒድ አስማረ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡

ባለ ዐሥር ወለሉ አዲስ ሕንጻ ከትምህርት ቤት ባሻገር መስጅድን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን የሚያካትት እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

የቀድሞው የአወሊያ ሁለገብ ሕንጻ ግንባታ በተለያዩ ጊዜያት ታቅዶ ሳይሳካ ቀርቶ እንደነበር በማስታወስ፣ “ያለፈውን ስህተት ላለመድገም” ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል። በዚህም መሠረት ግንባታው በቀጥታ በጠቅላይ ምክር ቤቱ እና በአወሊያ ቦርድ አመራሮች በጋራ ክትትል እንደሚደረግበትና ለዚህም 1 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተያዘ ተናግረዋል፡፡

የሕንጻ ንድፉ” በጥንቃቄ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ” የግንባታው መጀመርያ እና መጠናቀቂያ ጊዜ ይፋ እንደሚደረግ የተናገሩት አቶ ሰዒድ፤ በታሪካዊው የፒያሳው የአወሊያ ትምህርት ቤት ውስጥ በአሁኑ ወቅት እየተማሩ የሚገኙትን 350 ተማሪዎች በምትክ የሚሠራው ሕንጻ እስኪጠናቀቅ ድረስ ባሉበት ቦታ ትምህርታቸውን እንደሚቀጥሉ “ፕሮሚስ [ቃል] ተገብቶልናል” ብለዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በስሩ የታቀፈበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ድረ ገጽ ላይ የሰፈረው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ “በኢትዮጵያ የመጀመርያው የእስልምና ተቋም” አወሊያ የተመሠረተው በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1944 ነው፡፡ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እስከ  1968 ድረስ የግል ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ከ1969 እስከ 1985 ድረስ የማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ሆነ፡፡ ከ1985 በኋላ በትምህርት ሚኒስቴር እና በወርልድ ሙስሊም ሊግ መካከል በተደረገ ስምምምነት መሠረት ሥሙ ወደ “አወሊያ ሙስሊም ሚሲዮን ትምህርት ቤት” ወደሚል ተቀይሮ “ሴኩላር” እና ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በማደባለቅ መስጠት ጀመረ፡፡ ከ1996 እስከ 2003 ድረስ በሙስሊም ወርልድ ሊግ በሳዑዲ ዐረቢያ በተመሠረተው “ኢንተርናሽናል ኢስላሚክ ሪሊፍ ኦርጋናይዜሽን” (IIRO) ይደገፍ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ እስካሁን ድረስ በስሩ ያቀፈው ጠቅላይ ምክር ቤቱ ነው፡፡

ትምህርት ቤቱ በቅርብ ዓመታት “ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ አጋጥሞታል” በሚል በአደባባይ ድጋፍ ሲጠየቅለት የነበረ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular