“ሸሪክ” የተሰኘ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስጠት የሚታወቀው ዳሸን ባንክ፤ የባለአክሲዮኖች 33ኛ መደበኛ እና 29ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሄዷል።
ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 19/2019 እየተካሄደ በሚገኘው ጉባዔ ላይ የ2018 በጀት ዓመት የባንኩ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቧል።
በዚህ ወቅት የተናገሩት የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ፣ ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱን በማስፋት 16 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ማሠራጨት ተችሏል።
የሸሪዓ መርሆዎችን በመከተል ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፉ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ዕድገት የተመዘገበበት ሲሆን፣ ይህም 75 በመቶ ተጨማሪ ዕድገት የታየበት መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡ የደንበኞች ቁጥርም በ1 ነጥብ 35 ሚሊዮን ጭማሪ በማሳየት አሁን ላይ ወደ 9 ነጥብ 1 ሚሊዮን መድረሱን አክለዋል።
ዳሸን ባንክ በመላ ኢትዮጵያ 93 ቅርንጫፎቹ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል። አጠቃላይ የቅርንጫፎች ቁጥርም 900 መድረሱ ተጠቁሟል።
ባንኩ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ዘርፍ ያለው ተቀማጭ ሀብት አሁን ላይ 27 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መድረሱ በጠቅላላ ጉባኤው ወቅት ተገልጿል። ከተመዘገበው 350 ቢሊዮን የዳሽን ጠቅላላ ሀብት ውስጥ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ የተገኘው ባንኩ ከሚሰጠው የሸሪዓ መርሆዎችን መሠረት ካደረገው የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፍ መሆኑ በኃላፊዎቹ ተብራርቷል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የዳሸን ቦርድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዱላ መኮንን ባደረጉት ንግግር፣ ባንኩ በሁሉም የፋይናስ ዘርፎች ዘላቂ ዕድገት በማስመዝገብ ጥንካሬውን አሳይቷል ብለዋል። በፋይናንስ አፈጻጸም፣ በዲጂታል አገልግሎት ዕድገት፣ የደንበኞች ቁጥርን በማሳደግ፣ በሀብት ማሰባሰብና ኢንቨስትመንቶች ዘርፎች የተመዘገበው ውጤቶች የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ለተለያዩ
ለማኅበረሰብ ተኮር ተግባራት 200 ሚሊዮን ብር ፈሰስ አድርጓል ሲሉ አክለዋል። የባንኩ ባለአክሲዮኖች ቁጥርም ዕድገት እያሳየ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ዳሸን ባንክ ዛሬ ባካሄደው 33ኛ መደበኛ እና 29ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የባንኩ ባለአክሲዮኖች እና የሸሪዓ አማካሪ ቦርድ አባላት ተገኝተዋል። (ሚንበር ቲቪ)












