ዩናይትድ ኪንግደም በሱዳን አል ፋሸር ከተማ በተፈጸመው መጠነ ሰፊ የፆታዊ ጥቃት ዘመቻ እና የጅምላ ግድያ እጃቸው አለበት በተባሉ የሱዳን ባለሥልጣናትና ወታደራዊ አዛዦች ላይ አዲስ ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች። የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ የጉዞ እና የንብረት እገዳ ማዕቀቡ የተጣለው ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና ከሱዳን መደበኛ ጦር የተውጣጡ 15 አዛዦች ላይ ነው፡፡
የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤድ ሚሊባንድ እንዳሉት፤ አዲሱ ማዕቀብ በግጭቱ በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በተፈጸሙ “የጅምላ ጭፍጨፋ ወንጀሎች” የተጠረጠሩትን ኢላማ ያደረገ ነው።
በአል ፋሸር ከተማ የተፈጸሙት ጭፍጨፋዎች አንድ ዓመት መሙላቱን ያስታወሱት ኤድ ሚሊባንድ፤ በዩናይትድ ኪንግደም ድጋፍ የተደረጉ ምርመራዎች አስገድዶ መድፈር እና ረሃብ አሁንም በሱዳን ሕዝብ ላይ እንደ ጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
እነዚህ ድርጊቶች “በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች” መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ወንጀለኞች ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው እንዲሁም ለተዋጊ ወገኖች ከውጭ የሚደረግ ማንኛውም ድጋፍ መቆም እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።
ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፣ በሚያዝያ 2015 በሱዳን በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ግጭት በዓለም ላይ ትልቁን የሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ የአል ፋሸር ጅምላ ጭፍጨፋ በግጭቱ ሳቢያ ከተከሰቱት እልቂቶች አንዱ ነው።
የዬል የሰብአዊ ምርምር ላብራቶሪ አጥኚዎች የግድያው ፍጥነት ሊወዳደር የሚችለው ከሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ጋር ብቻ እንደሆነ ይገልጻሉ። በግጭቱ ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
በሱዳን ጦርነት እልቂት ያስተናገደችው በምዕራብ ሱዳን የዳርፉር ግዛት ዋና ከተማና የሰሜን ዳርፉር ክፍለ ሀገር አስተዳደር ማዕከል የሆነችው አልፋሸር፤ በ18ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ በዳርፉር እስላማዊ ሡልጣኔት ዘመን እንደ ዋና ከተማና የሡልጣኑ ቤተመንግሥት መቀመጫ ሆና የተመሠረተች ናት፡፡ የመጨረሻው የዳርፉር ሡልጣኔት መሪ ሡልጣን ዓሊ ዲናር፣ በአንደኛው ዓለም ጦርነት ወቅት መካ በኦቶማን ኢምፓየርና በሌሎች ግጭቶች ምክንያት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት፣ ከአልፋሸር በመነሳት ለካዕባ የሚሆን “ኪስዋ” በማዘጋጀትና በመላክ በታሪክ ይታወሳሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












