የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ) እድገት እየተፋጠነ ባለበት ወቅት በአፍሪካ አህጉር አሁንም 900 ሚሊዮን የሚጠጉ አፍሪካውያን ከመስመር ውጭ መሆናቸውን ይፋ ያደረገው የዓለም ባንክ አዲስ ሪፖርት ነው። ባንኩ “የአፍሪካ ኢኮኖሚክ መሻሻል፡ የኤአይ ዝግጁነትን መገንባት” በሚል በዚህ ወር ባወጣው ሪፖርቱ ላይ እንደጠቀሰው፣ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ከሰሐራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ በሚደረጉ ቻናሎች የኢኮኖሚ መሠረት እየሆነ መጥቷል።
ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ዕድገት በ2025 ከነበረበት 4.1 በመቶ በ2026 ወደ 4.3 በመቶ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል። ይህም ከባለፈው ሚያዝያ ወር 2018 ከነበረው ትንበያ የ 0.3 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ሪፖርቱ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ግጭት፣ የንግድ ፖሊሲ አለመረጋጋት፣ ጥብቅ የፋይናንስ ሁኔታ፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ወረርሽኝ እና አለመተማመን በበርካታ ሀገሮች ውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ፈተና ውስጥ መክተቱን አመልክቷል።
ይሁን እንጂ ይህ የኢኮኖሚ መሻሻል የመጣው በማክሮ ኢኮኖሚ ለውጦች፣ በሀገር ውስጥ ፍላጎት እና በዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር ኢንቨስትመንቶች በመደገፉ መሆኑንም ያትታል። በዚህም እንደ ኢትዮጵያ፣ አንጎላ፣ ናይጄሪያ እና ዛምቢያን ጨምሮ በቀጣናው ያሉ ሦስት አራተኛው ሀገሮች የመቋቋም አቅም ማሳየታቸው ለኢኮኖሚው መሻሻል ጠቀሜታው ተገልጿል።
እንደ ዓለም ባንክ ሪፖርት ከሆነ፣ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ እ.አ.አ እስከ 2035 ድረስ በአፍሪካ የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ላይ እስከ 1 ትሪሊዮን ዶላር በማደግ ከ35 እስከ 40 ሚሊዮን ዲጂታል ሥራዎች ሊጨ ወደ ገበያው ሊገቡ ይችላሉ። በዚህም በዓመት እስከ 150 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የግብር ገቢ ሊያስገኝ ይችላል።
ነገር ግን አህጉሪቱ ወደ ኤአይ ልማት እየገባች ያለችው ዝቅተኛ ምርታማነት፣ የሰው ኃይል እጥረት እና ደካማ የአገልግሎት አቅርቦትን ጨምሮ በኤሌክትሪክ፣ በግንኙነት፣ በክህሎት፣ በመረጃ እና በኮምፒዩተር መሠረተ ልማት ላይ ያሉ መሠረታዊ የልማት ክፍተቶችን ይዛ እንደሆነ አክሏል።
አህጉሪቱ ከዓለም ሕዝብ ወደ 18 በመቶ የሚሆነውን ብትይዝም የዓለም አቀፍ ዳታ ሴንተር አቅም ያለው 0.6 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው። ከእነዚህ ዳታ ማዕከላት 5 በመቶ ያህሉ ብቻ ለአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ዝግጁ ናቸው፡፡ ይህም አብዛኛው የአፍሪካ ሕዝብ ከዲጂታል እና ከሕዝብ አገልግሎቶች ሊገለል ይችላሉ የሚል ሥጋት እንዳለ ጠቁሟል። ከሰሃራ በታች ባሉ አፍሪካ ሀገራት ውስጥ የኤአይ ተቀባይነት በፍጥነት እያደገ ቢሆንም እድገቱ ያልተመጣጠነ እንደሆነ ሪፖርቱ ጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪ በሪፖርቱ የተካተተው ምንም እንኳን የኢኮኖሚ እድገቱ መሻሻል ቢያሳይም በመካከለኛው ምስራቅ የቀጠለው ግጭት የውጭ እርዳታ መቀነስ እና እንደ ኤልኒኖ ያሉ የአየር ንብረት ክስተቶች ዓለም አቀፍ የኃይል፣ የምግብ እና የማዳበሪያ ዋጋዎችን ከፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል ብሏል። ኤል ኒኖ በመጪዎቹ ወራት በምሥራቅ አፍሪካ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እና የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቁሟል።
በዓለም አቀፍ የኃይል መስተጓጎል የተነሳ የዋጋ ግሽበት በ2025 ከነበረበት 3.7 በመቶ በ2026 ወደ 5.5 በመቶ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሪፖርቱ አስቀምጧል። በመካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋት ሳቢያ የዓለም የኢነርጂ ዋጋ በ2026 እስከ 24 በመቶ እንዲሁም የማዳበሪያ ዋጋ እስከ 31 በመቶ ሊጨምሩ እንደሚችሉ የአለም ባንክ ትንበያውን አስቀምጧል።
የማዳበሪያ እና የነዳጅ ወጪዎች በኢኮኖሚው ውስጥ የምርት፣ የትራንስፖርት እና የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ከፍ እንዲሉ ማድረጉ የምግብ ዋስትናን አደጋ ላይ እንደሚጥለው አክሏል። (ሚንበር ቲቪ)












