እሑድ , ذو الحجة 17, 1445
Google search engine
Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችኢንዶኔዥያዊው ልዩ የሐጅ እንግዳ

ኢንዶኔዥያዊው ልዩ የሐጅ እንግዳ

የአላህ እንግዶች ዛሬም ወደተጠሩበት እየጎረፉ ይገኛሉ። በዘንድሮው የ1445ኛ ዓ.ሂ የሐጅ ሥርዓት እንደ አምናው በቁጥር በርካታ ምዕመናንን የምትልከው ኢንዶኔዥያ፣ ልጇን ሙሐመድ ኑር ፋይዚንም “በሰላም ግባ” ብላ ሸኝታዋለች። ሀገሪቱ ሙሐመድን ስትልከው ለብቻው አይደለም። ታናሽ ወንድሙ ተከትሎታል። ታናሽየው ዩሊያዋን ፋይዚን ይባላል። 43 ዓመቱ ነው፣ ከታላቁ በሁለት ዓመት ያንሳል።

ሙሐመድ እና ዩሊያዋን ለሐጅ ክንውን ሳዑዲ ዐረቢያ የደረሱት ሰሞኑን ነው። ታላቅ እና ታናሽ የመጀመሪያ መዳረሻቸው በሆነችው ቅድስት ከተማ መዲና ባንድነት ካልሆነ አይታዩም። በመንገዳቸው ታናሽየው ዩሊያዋን መሪ ነው። ታላቁን የፈለገበት ያደርሳል። ሲያስፈልግ ከእንቅፋት ተከላካይ ነው። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ይደግፋል። ዩሊያዋን ታላቁ የጠየቀውን ሁሉ ለመሙላት ይጥራል።

ወንድማማቾቹ በመንገድ ላይ ሲጓዙ ለተመለከታቸው ትኩረት መሳባቸው አይቀርም። ታላቅ ሙሐመድ፣ የታናሽየው እገዛ ያስፈለገው የዓይን ብርሃኑ ስለተጋረደ ነው። ቢሆንም ሙሐመድ በወንድሙ አጋዥነት ለአላህ ጥሪ “ለበይክ” ለማለት ታድሏል። ሁሉንም የሐጅ ሥነ ሥርዐት ለመከወንም ናፍቋል።

በርግጥ ሙሐመድ እንደቀድሞ ውጥኑ ቢሆን ኖሮ ይህን ናፍቆት የሚወጣው ከሦስት ዓመት በፊት ነበር። አልተሳካለትም። በጊዜው ለመቅረቱ ሰበብ የነበረው ኮሮና ወረርሽኝ ነው። ሙሐመድ በወቅቱ ወደ ሐጅ ሊጓዝ የነበረው ባለቤቱን ብቻ አስከትሎ ነበር። ዘንድሮ ግን ባለቤቱ ብቻ ሳትሆን ዩሊያዋንም አብሮት አለ።  ታናሽየውም ቢሆን አልሰመረለትም እንጂ ለሐጅ የተነሳው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር። በዘንድሮ ሐጅ ወንድማማቾቹ ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር የዘመናት ምኞታቸው ሰምሯል።

ዩሊያዋን ታላቅ ወንድሙን መንገድ እየመራ ሲሄድ ላገኙት ዱዓ እንዲያደርጉለት መጠየቅ ልማዱ ነው። ዱዓው ወንድማማቾቹ የሐጅ ክንውናቸውን በብርታት እንዲፈፅሙ የሚደረግ መሆኑን የኤንዶኔዥያ መገናኛ ብዙኃን አስነብበዋል።

እንደ ሙሐመድ ሁሉ በቅድስቲቱ መዲና ከተማ የዓይን ብርሃናቸው የተጋረደ ምዕመናን ለአላህ ጥሪ “አቤት” ሊሉ እየተጓዙ ነው። የሐጅ መስተንግዶው ባለቤት ሳዑዲ ዐረቢያም ከ2018 አንስቶ ለሙሐመድ ዐይነት የአላህ እንግዶች አጋዥ ነው ያለችውን ታዘጋጃለች። ሙሐመድ ቁርኣን መቅራት ቢፈልግ የብሬል ቁርኣን አለ።

ሳዑዲ ዐረቢያ ለእነሙሐመድ ብቻ ሳይሆን መናገር ለሚሳናቸው ሑጃጆች የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎችን፣ መራመድ ለሚቸግራቸው ምዕመናን ደግሞ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ዊልቼር አዘጋጅቻለሁ ብላለች። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Google search engine

Most Popular

Recent Comments