Homeዜናና ወቅታዊዜናየባንኮች የሸሪዓ አማካሪ ሥያሜ እና ሚና ላይ ለውጥ እንዲደረግ ተጠየቀ

የባንኮች የሸሪዓ አማካሪ ሥያሜ እና ሚና ላይ ለውጥ እንዲደረግ ተጠየቀ


በኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ የሚገኙ የባንኮች የሸሪዓ አማካሪ ሥያሜ እና ሚና ላይ ለውጥ እንዲደረግ የተጠየቀው በዓመታዊ የሸሪዓ አማካሪዎች ጉባዔ ላይ ነው፡፡ ጉባዔው ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 17/2016 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ተካሄዷል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትን ጨምሮ የተለያዩ ባንኮች መሪዎች፣ የባንኮች የሸሪዓ አማካሪዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፋይናንስ እና ባንክ ዘርፍ ባለሞያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በጉባዔው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም፣ የመድረኩ ትኩረት ስለነበረው የሸሪዓ አማካሪዎች ጉዳይ አንስተው ንግግር አድርገዋል፡፡ ሸይኽ ሐጂ የሸሪዓ አማካሪዎችን በተመለከተ ከሌሎች ሀገራት ልምድ መቅሰም እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ በሥያሜው ላይ እንዲሁም የአማካሪዎቹ ሚና ላይ ለውጥ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት የሸሪዓ አማካሪ ቦርዱ አማካሪ የሚለውን ሥያሜው “ተቆጣጣሪ” በሚል መተካት እንዳለበት አማራጭ ያሉትን አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ ሸይኽ ሐጂ የሸሪዓ አማካሪዎች ሥያሜ በተቆጣጣሪ መተካቱ “ሚናቸውን ከፍ ሊያደርግ” የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በዛሬው ጉባዔ መድረክ ላይ ከወለድ ነጻ የፋይናንስ አገልግሎት በኢትዮጵያ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አስመዝግቧል የተባሉ ለውጦች ተነስተዋል፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ባንኮች ውስጥ ተቀማጭ ከተደረገው ገንዘብ 10 በመቶ የሚሆነው መጠን የወለድ ነጻ ባንኮች መሆኑም በዚሁ ጉባዔ ላይ ተገልጧል፡፡

በጉባዔው ላይ የሸሪዓ አማካሪዎችን ሚና የተመለከተ የፓናል ውይይት እና በእስላማዊ ፋይናንስ ላይ ያጠነጠነ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡ በመድረኩ ላይ “የወለድ ነጻ የፋይናንስ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ እና ቀጣይ ተስፋዎቹ” በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት አቶ ዓብዱልቃድር ሬድዋን ናቸው፡፡

በተመሳሳይ በተሰናዳው የፓናል ውይይት ላይ ከተለያዩ ባንኮች የተውጣጡ ባለሞያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከተሳታፊዎቹ ውስጥ ኡስታዝ ማሕሙድ ሐሰን፣ ወይዘሮ መሊካ በድሪ፣ አቶ ኑር ሑሴን፣ አቶ ፍሬዘር አያሌው፣ አቶ ጥበቡ ተስፋዬ፣ አቶ ዓብዱልቃድር ሬድዋን እና ዶክተር ዐብደ ዓሊ ይጠቀሳሉ፡፡

ዓመታዊውን የሸሪዓ አማካሪዎች ጉባዔ ያዘጋጀው የኢትዮጵያ የወለድ ነጻ የፋይናንስ ባለሞያዎች ማኅበር፣ 2013 የተመሠረተ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከወለድ ነጻ የፋይናንስ አገልግሎትን በማሳደግ የመሪነት ሚና የመጫወት ዓላማ ያለው ማኅበሩ፣ በዘርፉ የረዥም ጊዜ ልምድ ያካበቱ ባለሞየዎችን አባልነት ያቀደፈ መሆኑን ይናገራል፡፡


RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular