የቱርክ መዲና ኢስታንቡል በእስላማዊ ፋይናንስ ላይ የሚያተኩረውን አል-በረካ ጉባዔ ከትናንት ጁመዓ ጀምሮ እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ ዛሬ በሚጠናቀቀው ጉባዔ ላይ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን ተገኝተው ዓለም የምትመራበት ሥርዐት በድጋሚ ሊቃኝ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የአል-በረካ ጉባዔ ትናንት ሲጀመር፣ በመክፈቻው ላይ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ላይ አጽንኦት የሰጡበት ጉዳይ የወቅቱ የዓለም የኃይል አሰላለፍ ነው፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ዓለማችን ከፍተኛ ለውጥ እያካሄደች ነው ያሉት ኤርዶጋን፣ ይህን በግልጽ ማየት እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ዓለም አቀፉ ሥርዐት ሚዛኑን ማጣቱን እንዲሁም የወቅቱ የዓለም መልክ የሚገለጸው በሁከት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ኤርዶጋን በዚህም ምክንያት ዓለም አቀፉ ሥርዓት አሁን ካለው ሁኔታ ጋር በሚስማማ መልኩ እንደገና መቃኘት አለበት ብለዋል፡፡ ዓለም ከተጨቆኑ ጎን መቆም እንዳለበት በመጠቀም፣ የጋዛን ጉዳይ በምሣሌነት አንስተዋል፡፡
ለሁለት ቀን የሚቆየው የአልበረካ ጉባዔ፣ በኢስላማዊ ፋይናንስ ዘርፍ ላይ ያለውን ሞያዊ ዕውቀት ከእስላማዊ ሀገራት ጋር ለማስተሳሰር ያለመ ነው ተብሏል፡፡ ከ75 የተለያዩ ሀገራት ወደ ኢስታንቡል ያቀኑ ተሳታፊዎች በተገኙበት መድረክ ላይ ከ1 ሺሕ 500 በላይ ግለሰቦች ታድመውበታል፡፡

ባለሞያዎችን፣ ምሁራንን፣ የፖሊሲ እና የኢንዱስትሪ መሪዎችን በማሰባሰብ በእስላማዊ ኢኮኖሚ ውስጥ ያሉ ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮችን፣ አዝማሚያዎችን እና ዕድሎችን ለመወያየት እንዲሁም ዘላቂ ዕድገትን እና ፈጠራን ለማሳለጥ ያስችላል በተባለው መድረክ፣ 35 የዘርፉ ኤክስፐርቶች ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ የእስላማዊ ፋይናንስ ዕድሎች እና ስጋቶች ላይ ያተኮሩ የጥናት ወረቀቶች ቀርበው ውይይት ተካሄዶበታል፡፡ በመድረኩ ላይ ከተነሱ ርእሰ ጉዳዮች ውስጥ ስለ ዘካ አጠቃቀም እንዲሁም የእስላማዊ ኢንቨስትመንት ተመክሮ ይገኝበታል፡፡ የአልበረካ ጉባዔ ዛሬ ቅዳሜ እንደሚጠናቀቅ የቱርክ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል፡፡












