Homeዜናና ወቅታዊዜናየኒውዮርክ ከንቲባ ለከተማዋ የሚቀርቡ ምግቦች ለሐላል የአመጋገብ ሥርዓቶች ምቹ እንዲሆኑ የሥራ አስፈጻሚ...

የኒውዮርክ ከንቲባ ለከተማዋ የሚቀርቡ ምግቦች ለሐላል የአመጋገብ ሥርዓቶች ምቹ እንዲሆኑ የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ፈረሙ

በአሜሪካ የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ዞህራን ማምዳኒ፤ በሕዝብ በጀት የሚደገፉ የምግብ አቅርቦት ፕሮግራሞች የሃይማኖት አመጋገብ ሥርዓቶችን በተለይም ሐላል ምግቦች በተሻለ እና በወጥነት እንዲቀርቡ የሚያደርግ የአስፈጻሚ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

ከንቲባ ማምዳኒ አስፈጻሚ ትዕዛዙን ኅዳር 9፤ 2019 በፈረሙበት ወቅት፤ “የከተማዋ መሥሪያ ቤቶች የሚያቀርቧቸው ምግቦች ከተማዋን እንደ ቤታቸው የሚቆጥሩ ነዋሪዎችን የሚያንጸባርቁ መሆን አለባቸው፤ ማንኛውም የኒውዮርክ ነዋሪ የሃይማኖት ሥርዓቱን ስለሚጻረር ብቻ ገንቢ ምግብን ሳይቀበል መቅረት የለበትም” ብለዋል።

የኒውዮርክ ከተማ መሥርያ ቤቶች በየዓመቱ ለተማሪዎች፣ ለሆስፒታል ታካሚዎች፣ ለአረጋውያን፣ በመጠለያ ለሚገኙ ነዋሪዎች እና ለሌሎች ዜጎች ከ220 ሚሊዮን በላይ ምግቦችን እና መክሰሶችን ያቀርባሉ። ከዚህ ቀደም የሃይማኖት አመጋገብ ጥያቄዎች እንደ ኤጀንሲው ልዩነት እና በጥያቄ ብቻ የሚስተናገዱበት ሁኔታ እንደነበር ተገልጿል።

አዲሱ ትዕዛዝ የከተማው የምግብ ፖሊሲ ቢሮ በከተማ አቀፍ ደረጃ የምስክር ወረቀት ደረጃዎችን፣ ግልጽ የምግብ እና የግብዓት መለያዎችን እንዲሁም ዓመታዊ የተጠቃሚዎች ዳሰሳን የሚያካትት ወጥ መመሪያ እንዲያዘጋጅ ያዛል። የከተማዋ ኤጀንሲዎች አዲሱን ደንብ ተግባራዊ ለማድረግ የአንድ ዓመት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል። ከንቲባው ከሐላል በተጨማሪ የአይሁድ ምግብ የሆነው “ኮሸርን”ም በተመሳሳይ መልኩ እንዲቀርብ ፈቅደዋል።

የኤፒክሴንተር ኤንዋይሲ ዘገባ እንዳመለከተው፤ ሐላል አመጋገብን የሚከተሉ የኒውዮርክ ነዋሪዎች ከምግብ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ሲወጡ የቀረቡት አማራጮች ሃይማኖታዊ የምግብ ሥርዓታቸውን የማያሟሉ በመሆናቸው ከሌሎች ያነሰ ምግብ ይዘው ወይም ፕሮቲን ሳያገኙ ይወጡ ነበር፡፡

በከተማዋ ከተጠኑ 75 የምግብ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ውስጥ ሐላል ምግብ የሚያቀርቡት 38 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ዘገባው አመልክቷል። የከንቲባው ውሳኔ ነዋሪዎች ፕሮቲን ወይም የተሟላ ምግብ ሳያገኙ የሚቀሩባቸውን ዓመታት ያስቆጠሩ ችግሮች ለመፍታት ያግዛል ተብሏል።

የሜትሮፖሊታን ኒውዮርክ ሹራ ፕሬዝዳንት ኢማም ዓብዱላህ፣ የሐላል ምግቦች ተደራሽነት ብቻ ሳይሆን በታመኑ አካላት የተረጋገጡ፣ ብክለት የሌለባቸው እና በጠንካራ ክትትል ሐላል መሆናቸው የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular