የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ በመዲናዋ እድሜቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት በዘመቻ ሊሰጥ መሆኑን አስታውቋል። ቢሮው ዛሬ ሐሙስ ኅዳር 10፤ 2019 ባወጣው መግለጫ ክትባቱ ከነገ ጁመዓ ኅዳር 11 እስከ ኅዳር 14፤ 2019 የሚቆይ ነው።
ቢሮው እንዳስታወቀው፣ ለ4 ተከታታይ ቀናት የሚቆየው የክትባት ዘመቻ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ሁሉም ሕፃናት የሚሰጥ ነው፡፡ ሕጻናቱ ከዚህ ቀደም ቢከተቡም ባይከተቡም ይወስዳሉ ብሏል። ክትባቱ የሚሰጠው ቤት ለቤት፣ በመጠለያ ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በቅድመ መደበኛ እና በሕፃናት ማቆያዎች እንዲሁም ሕፃናት በሚገኙበት ቦታዎች እንደሆነ ገልጿል።
የልጅነት ልምሻ ቫይረስ በተበከለ ምግብና ውሃ አማካኝት የሚመጣ እና ሕፃናትን ለዘላቂ የእጅ፣ እግርና የአካል መልፈስፈስ (ሽባነት) የሚያስከትል ሲሆን፣ ሕጻናትን ለሞትም የሚዳርግ አደገኛ በሽታ ነው።
በሽታውን መከላከል የሚቻለው በመደበኛ እና በዘመቻ መልክ በሚሰጥ ክትባት ብቻ እንደሆነ የገልለጸው ቢሮው፣ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች እድሜያቸው እሰከ 5 ዓመት ያሉ ሕጻናትን በማስከተብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል። (ሚንበር ቲቪ)












