የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ በሀገሪቱ ለሚገኙ ኢስላማዊ ባንኮች ሊኩዲቲ አስተዳደር የሚሆን የወለድ ነፃ ራሱን የቻለ አዲስ የሕግ ማዕቀፍ መመሪያ አጽድቋል። መመሪያው ከእስላማዊ የባንክ መርሆች ጋር የሚጣጣሙ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያዎችን ለማዘጋጀት እና ወደፊት ለሚመጡት የእስላማዊ ግምጃ ቤት ሰነዶችን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ነው፡፡
ይሁን እንጂ የእስላማዊ የግምጃ ቤት ሰነዶች እና የመንግሥት ሱኩክ ወደ ገበያው ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ቢገለጽም እስካሁን ይፋ አልተደረገም።
ይፋ የሆነው ከወለድ ነፃ ክፍት የገበያ እንቅስቃሴዎች እና ቋሚ አገልግሎቶች መመሪያ ቁጥር EPD/01/2026፣ መደበኛ እና ወለድ ተኮር የሆኑ አሠራሮች ላይ ያልተመረኮዘ የገንዘብ እንቅስቃሴዎችን ለማካሄድ የሚያስችል መሠረት የሚጥል ነው።
ብሔራዊ ባንክ ያወጣው አዲሱ የሕግ ማዕቀፍ ተሳታፊ ተቋማት የሸሪዓ ሕጎችን ባከበረ መልኩ የአጭር ጊዜ የፋይናንስ ፍላጎቶቻቸውን እንዲያሟሉ እና ትርፍ ሊኩዲቲያቸውን እንዲያስተዳድሩ ያግዛል ተብሏል። እንዲሁም በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ውስጥ የገንዘብ ፖሊሲ ውሳኔዎችን ለማጠናከር እንደሚረዳ ተገልጿል።
መመሪያው በኢትዮጵያ እያደገ ለሚገኘው የወለድ ነጻ የባንክ ዘርፍ በባንኮች መካከል የሚደረጉ ግብይቶችን ጨምሮ ለሰፊው የእስላማዊ የገንዘብ ገበያ እድገት የሚያግዝ እንደሆነም ተጠቅሷል።
ብሔራዊ ባንክ በተያዘው ዓመት መጀመርያ ተገቢ በሆኑ ደንቦች፣ በሸሪዓ አስተዳደር፣ በፋይናንስ ምርቶች እና በተቋማዊ አቅም የተደገፈ የፋይናንስ ሥነ ምሕዳርን ለመፍጠር ያለመ የ2026-30 ‘ብሔራዊ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ስትራቴጂ’ን ይፋ አድርጓል።
ስትራቴጂው የሀገሪቱን የተካፉል (የእስላማዊ ኢንሹራንስ) ዘርፍ እና የካፒታል ገበያን ለማልማት ያስችላል የተባለ ሲሆን የእስላማዊ የፋይናንስ ግብይቶች የታክስ አሠራርን፣ የሰው ኃይል ልማትን እና የእስላማዊ ማይክሮፋይናንስን እንዲሁም የእስላማዊ ፊንቴክ ጉዳዮችን ያካተተ ነው። (ሚንበር ቲቪ)












