የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ በዘንድሮ 1448 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ስምንት ሺሕ ምዕመናንን ለመመዝገብ በእቅድ መያዙ ተገልጿል፡፡ ይህ የተገለጸው የጠቅላይ ምክር ቤቱ ሐጅና ዑምራ ዘርፍ ከሥነ ሥርዐቱ አገልግሎት አቅራቢ ከሳዑዲ ዐረቢያው መሻሪቅ አልማሲያ ጋር የስምምነት ሰነድ በተፈራረመበት ወቅት ነው፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ዛሬ ሰኞ መስከረም 25/2019 ባሠራጨው መረጃ እንዳመለከተው፤ የስምምነት ሰነዱ የተፈረመው በመካ ከተማ ነው፡፡ የጠቅላይ ምክር ቤቱ የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ሙሐመድ ሷሊህ እና የመሻሪቅ አልማሲያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በንደር ቢን ዓብዱረሕማን አልደመንሁሪ ተፈራርመዋል።
የውል ስምምነቱ ዘንድሮ በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ለሚሳተፉ ስምንት ሺሕ ኢትዮጵያውያን ሑጃጅ የሚሰጡ አገልግሎቶችን “በተቀናጀ መልኩ ጥራታቸውን የጠበቁ፣ ደህንነታቸው የተረጋገጠ እና ተጠያቂነት የሰፈነባቸው ለማድረግ ያለመ” ነው።

የዘርፍ ኃላፊው እንደገለጹት፣ ከመሻሪቅ አልማሲያ ጋር የተደረሰው ስምምነት የቅድመ ዝግጅት ስራው አካል ነው፡፡ ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ጋር ስምምነት የተፈራረመው መሻሪቅ አልማሲያ ለኢትዮጵያውያን ምዕመናን የባለፈውን ዓመት የሐጅ መስተንግዶ ያቀረበ ኩባንያ መሆኑ ታውቋል፡፡ አልማሲያ ለደቡብ ምሥራቅ እስያና ከሌሎችም ቀጣናዎች ለሚጓዙ ሑጃጅ አገልግሎት ሰጪ ነው፡፡ ኩባንያ የሚሰጠው አገልግሎት ከሎጂስቲክስ አቅርቦት ጀምሮ የመግቢያ በሮች አቀባበል፣ የቅዱሣን ሥፍራዎች ጉብኝትና የምግብ አቅርቦትን ያካትታል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ባለፈው ዓመት በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ የሚሳተፉ ስድስት ሺሕ ምዕመናንን ለመመዝገብ አቅዶ ወደ ቅዱሣኑ ሥፍራዎች የተጉጓዙት 5 ሺሕ 210 መሆናቸው ይታወቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)
ፎቶ፡ ፋይል እና EIASC












