የአሜሪካዋ ካሊፎርንያ ሁለቱን እስላማዊ በዓላት ዒድ አል ፊጥር እና ዒድል አል አድሓን የግዛት በዓላት አድርጋ በመቀበል ሁለተኛዋ የሀገሪቱ ግዛት ሆናለች፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ማት ሄኒ የቀረበው የሕግ ረቂቅ፤ በሀገረ ገዥው ፊርማ በመጽደቁ የግዛቱ ሠራተኞች በእነዚህ ቀናት በበዓል ፈቃድ ከሥራ ነጻ መሆን ይችላሉ፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ማት ሐኒ፣ “ካሊፎርንያ በሀገሪቱ ትልቁ እና የነቃ ተሳትፎ የሚያደርግ ሙስሊም ማኅበረሰብ የሚኖርባት ቦታ ነች” ብለው ነበር፡፡ ረቂቁ የካሊፎርንያ ሙስሊሞች “በጉልሕ እንዲታዩ፣ ዋጋ እንዲሰጣቸው እና በግዛታችን ውስጥ እንዳለው ማንኛውም ማኅበረሰብ ሁሉ በተመሳሳይ ክብር እንዲስተናገዱ ለማድረግ ያለመ” መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡
የሕግ ረቂቁ ከመጽደቁ በፊት ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ በምክር ቤት ቀርቦ በ64 ለ 1 ድምጽ ያለፈ ሲሆን፣ በኋላም የሴኔት ድምጽ አግኝቷል፡፡ ሕጉ በመጽደቁ ሁለቱ የበዓል ቀናት ግዛቷ እውቅና ከሰጠቻቸው እንደ ዲዋሊ እና የጨረቃ አዲስ ዓመት ያሉ የማኅበረሰብ አቀፍ በዓላት ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፡፡
በአሜሪካ በርካታ ግዛቶች እና ከተሞች ዒድን በአካባቢ ደረጃ ዕውቅና ይሰጣሉ እንጂ እንደ ግዛት በዓል አይቀበሉትም፡፡ ከዚህ ቀደም የዋሺንግተን ግዛት የመጀመርያው በመሆን እ.አ.አ በ2015 ሁለቱን በዓላት የግዛት በዓላት አድርጓል፡፡
ሕጉ መጽደቁን ተከትሎ አስቀድሞም ሲሟገት የቆየው ዘ ካውንስል ኦን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ፤ ገዥው ሕጉ ላይ መፈረማቸውን በአድናቆት ተቀብሎታል፡፡ ይህ ውሳኔ በግዛቱ ውስጥ የሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሙስሊም ነዋሪዎችን ሃይማኖታቸውን ከመከወንና ለሥራ ወይም ለትምህርት ከመገኘት መካከል አንዱን እንዲመርጡ ግዴታ ውስጥ የሚጥላቸውን ለዓመታት የቆየ ፈተና ያነሳላቸዋል ብሏል፡፡ ዘ ካውንስል ኦን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ አክሎም፤ እነዚህን በዓላት በይፋ ዕውቅና መስጠት ካሊፎርንያ እያደገ ከመጣው ጥላቻ አንጻር የሙስሊሙን ማኅበረሰብ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተውና እንደሚጠብቀው ጠንካራ መልዕክት ያስተላልፋል ብሏል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












