Homeዜናና ወቅታዊዜናኔታንያሁ በምስጢር ወደ ኤሚሬትስ የተጓዙት ለምንድን ነው?

ኔታንያሁ በምስጢር ወደ ኤሚሬትስ የተጓዙት ለምንድን ነው?

ከእስልምና ቅዱሣን ሥፍራዎች አንደኛው በሆነው መስጂደል አቅሷ እንዲሁም ሰፊውን የፍልስጤም ግዛት በወረራ በመያዝ በንጹሐን ላይ ግድያ እና በርካታ ስቅይት በመፈጸም በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስር መያዣ የተቆረጠባቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ባለፈው እሑድ በምስጢር ወደ ተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ አቡ ዳቢ ተጉዘው ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሙሐመድ ቢን ዛይድ አል ናሕያን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን አስቀድመው መረጃ ቢያወጡም፣ የተባበሩት ዐረብ ኤሚሬትስ መንግሥታዊ የዜና ወኪል ማረጋገጫ የሰጠው ውሎ አድሮ ሰኞ ምሽት ነበር፡፡ የዜና ወኪሉ ቢን ዛይድ ከኔታንያሁ ጋር ተገናኝተው “የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ውይይት አካሄደዋል” ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ዝርዝር ጉዳዮችን ይፋ አላደረገም፡፡

አሶሼትድ ፕረስ ይዞት እንዳወጣው ዘገባ ከሆነ ግን ከአንድ ወር በኋላ ሥልጣናቸው ስለሚያበቃ ሌላ ዙር የምርጫ ፉክክር ከተቀናቃኞቻቸው ጋር የሚጠብቃቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ወደ አቡ ዳቢ በምስጢር ያቀኑት የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንትን ውለታ ለመጠየቅ ነው፡፡ ይህ ውለታ መስከረም 26/2016 (እ.አ.አ ኦክቶበር 7/2023) ሐማስ ድንገተኛውን ኦፕሬሽን ከማድረጉ አስቀድሞ ቢን ዛይድ ለኔታንያሁ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን “በአደባባይ ክደው እንዲመሰክሩላቸው” ለመጠየቅ ነው፡፡

ፕሬዝዳንት ሙሐመድ ቢን ዛይድ በወቅቱ ለኔታንያሁ ስለ ጉዳዩ አስቀድመው ማሳወቃቸውን የዘገበው ሀአሬትዝ የተባለው የእስራኤል ጋዜጣ ነበር፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ፤ ቢን ዛይድ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት ከኦፕሬሽኑ ከዐስር ቀን በፊት ነው፡፡ ለ45 ደቂቃ በቆየው የስልክ ንግግር ቢንዛይድ ለኔታንያሁ ኦፕሬሽኑ የተቀነባበረው በጥቅምት 2017 ሐማስ “ሰማዕት ሆነዋል” ባላቸው ያህያ ሲንዋር አማካኝነት መሆኑን ነግረዋቸዋል፡፡ ኦፕሬሽኑ ከተፈጸመ ቀጣናውን እንደሚያምሰው ቢን ዛይድ አክለው አስጠንቅቀዋል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት የሀአሬትዝን ዘገባ በማስተባበል ዜናውን “ሐሰተኛ” ሲል ፈርጆት ነበር፡፡ በዚህ ሳይገታ ዜናው “ፖለቲካዊ መነሻ” ያለው መሆኑን በመጥቀስ ክስ እንደሚመሠርት አስታውቋል፡፡ ያን ጊዜ መረጃውን ያጋለጠው ጋዜጣው አሁንም ቢን ዛይድ እና ኔንታንያሁ በአውሮፕላን ማረፊያ ተገናኝተው ስለዚህ ጉዳይ መነጋገራቸውን አረጋግጧል፡፡

ከእስራኤሉ ጋዜጣ በተጨማሪ በወቅቱ ዎልስትሪት ጆርናል እና ዘ አትላንቲክ የግብጽ የሥለላ መሥሪያ ቤት በተመሳሳይ ስለ ሐማስ ኦፕሬሽን ከሦስት ቀን አስቀድሞ ለእስራኤል መረጃ መስጠቱን ዘግበው ነበር፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መረጃውን ያጋሩት የቀድሞው የግብጽ የሥለላ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ዓባስ ካሚል ናቸው፡፡ ሆኖም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በተለይ የሀአሬትዝን መረጃ ምንጭ ከፈትሕ እና ሐማስ ጋር ጠበኛ የሆኑት የፍልስጤሙ ፖለቲከኛ ሙሐመድ ደሕላን ናቸው በሚል አጣጥለውታል፡፡ ደሕላን ለተባበሩት ዐረብ ኤሚሬትስ ባላቸው ቅርበት የሚታወቁ ሰው ናቸው፡፡

በተባበሩት ዐረብ ኤሚሬትስ እና እስራኤል መካከል ያለውን ግንኙነት መደበኛ ያደረገው እ.አ.አ በ2020 በአሜሪካ ፕሬዝዳንት አግባቢነት ከተፈረመው “የአብርሃም ስምምነት” በኋላ ነው፡፡ በእስራኤለ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሃካቢ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር እንደተናገሩት፤ እስራኤል ሊሰነዘሩ የሚችሉ የኢራን ጥቃቶችን ለመከላከል በራዳር የሚመራውን እጅግ ዘመናዊውን የአየር መከላከያ “አይረን ዶም” ለተባበሩት ዐረብ ኤሚሬቶች ልካለች፡፡

የኔታንያሁ ድንገተኛ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ ጉዞ በተሄደበት በዚህ ሰዓት በእስራኤል አንድ ወር ለቀረው ምርጫ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በተቀናቃኞቻቸው መካከል በአደባባይ የጦፈ ክርክር እየተደረገ ይገኛል፡፡ የእስራኤል አምስት ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ኔታንያሁን ከሥልጣን የማውረድ ዕድላቸውን ከፍ ለማድረግ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡ የእስራኤል ባለሥልጣናት በምርጫው ትኩረታቸው ቢወሰድም በፍልስጤማውያን ላይ ጥብቅ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ቀጥለዋል፡፡ የእስራኤል ሰፋሪዎች በጽንፈኛ ፖለቲከኞችና በፖሊስ ታግዘው በመስጂደል አቅሷ ላይ የሚፈጽሙትን ወረራም እንዲሁ ቀጥለውታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular