Homeዜናና ወቅታዊዜናየሚኒስትሮች ምክር ቤት የፌዴራል ገቢ ግብር ማሻሻያ ደንብን በሙሉ ድምጽ አጸደቀ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፌዴራል ገቢ ግብር ማሻሻያ ደንብን በሙሉ ድምጽ አጸደቀ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ መስከረም 18/2019 ባካሄደው 59ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ከእነዚህም መካከል የፌዴራል ገቢ ግብር ማሻሻያ ደንብ ላይ “በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል” በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

ምክር ቤቱ ባሰራጨው መረጃ እንዳመለከተው፤ ደንቡ የፌዴራል የገቢ ግብር ግልጽነትንና አስተዳደራዊ ቅልጥፍናን ለማረጋገጥ እና ከተሻሻለው የፌዴራል ገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ እንዲቻል የቀረበ ነው፡፡

ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም የአስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት አካሄዷል፡፡ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት እና ምርጫ ሕግ በየአምስት ዓመቱ የሚደረገውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 56 መሰረት አዲስ የአስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ማደራጀት የሚጠበቅ በመሆኑ፣ በ2018 ዓ.ም በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን በአዲስ መልክ ለማቋቋም እንዲያስችል ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

ምክር ቤቱ የተወያየበት ሌላኛው ጉዳይ በብሔራዊ የዳታ አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በረቂቁ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር በተፈረመው ለኃይል ሴክተር ሪፎርም፣ ኢንቨስትመንትና ዝመና ምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የአንድ መቶ አርባ አምስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺ ኤስ.ዲ.አር ብድር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ተወያይቷል፡፡ ምክር ቤቱም ስምምነቱ ከሀገራችን የብድር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም መሆኑን በማጋገጥ ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ተቋሙ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 87 ድንጋጌዎች መሰረት የተሰጡትን ሃገራዊ ተልዕኮዎች በህግ አግባብ ለመፈፀም እንዲችል የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 1286/2015 ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ውሳኔ ማሳለፉን የጥዕቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular