በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው አወሊያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በሚያካሄደው የስፖርት እንቅስቃሴ የሚታወቀው አወሊያ የዳዕዋ እና ስፖርት ክለብ፤ የምሥረታውን አርባኛ ዓመት ዛሬ እሑድ መስከረም 17፣ 2019 የስፖርት ማኅበሩ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት አክብሯል፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ የስፖርት ማኅበሩ ባለፉት አርባ ዓመታት ወጣቶችን በስፖርት እና በሥነ ምግባር በማነጽ እንዲሁም ያበረከተውን ማኅበራዊ ፋይዳ በተመለከተ ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህም የስፖርት ማኅበሩ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የፓናል ውይይት እና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡
ስለ ስፖርት ማኅበሩ የተጻፉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ለአወሊያ ስፖርት እና ዳዕዋ ክለብ ምሥረታ መነሻ የሆነው በ1970ዎቹ አጋማሽ በአዲስ አበባ ኳስ ሜዳ አካባቢ በሚገኘው “መርከዝ” ጓሮ ላይ በሚገኝ በጠባብ ሜዳ ላይ “የመርከዝ ቤተኞች” የነበሩት አቡበከር ዓብዱረሕማን፣ ናስር ማሕሙድ፣ በድሪ ሙሐመድና ሐጅ ሙሐመድ ይማም እንዲሁም ሌሎችም በመሆን ያስጀመሩት የእግር ኳስ ጨዋታና የሰውነት ማጎልመሻ እንቅስቃሴ ነው፡፡
በዚህ እንቅስቃሴ ላይ የሚሳተፉ ወጣቶች ቁጥር በመበራከቱ “በሜዳ ጥበት” ሳቢያ ከመርከዝ ብዙም የማይርቅ ቦታ ሲፈልጉ ወደ አወሊያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛውረው እስካሁንም ድረስ የስፖርት እንቅስቃሴውን ሊቀጥል ችሏል፡፡ ይህን ሜዳ ለመጠቀም ለትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጥያቄውን ያቀረቡት ሐጂ ሙሐመድ ይማምና ዓብዱረሕማን ሐጂ ሙሐመድ አሕመድ ናቸው፡፡
በስሩ በርካታ ወጣቶችን ያቀፈው የስፖርት ክለቡ፤ በተለያየ ጊዜ በኢትዮጵያ ቡድን በመጫወት ያሳለፉ ተጫዋቾችን ማፍራት ችሏል፡፡ ከእነዚህም መካከል የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ዓሊ ረዲ፣ ሳዳት ከማል፣ ሙሐመድ ኪንግ፣ ኻሊድ ሙሐመድ፣ ዑመር ዓብደላ፣ ኢብራሂም ሑሴን ይጠቀሳሉ፡፡ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ አማካይ ሐይደር መንሱር፣ የቀድሞው የመድን ተጨዋች ዓብዱልፈታህ ናስር እንዲሁም የመብራት ኃይሎቹ አንዋር ያሲን እና አንዋር ሲራጅም በዚሁ ክለብ አልፈዋል፡፡
አወሊያ የዳዕዋ እና ስፖርት ክለብን ለረዥም ዓመታት በመምራት ረገድ በአሁኑ ሰዓት በሕይወት የሌለውና ለሕንጻ ኮንስትራክሽን የተጫወተው እስማኤል አሕመድ እና በታላቁ አንዋር መስጂድ ለበርካታ ዓመታት ዳዕዋ በማድረግ የሚታወቁት ሸይኽ ያሲን ሰልማን በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)
(ለዚህ ዘገባ የቢላል መጽሔት 2ኛ ዓመት ቁጥር 1 መስከረም 1986 ዕትም በዋቢነት ጥቅም ላይ ውሏል)
የፎቶ ምንጭ፡ ሀሩን ሚዲያ እና SM












