የኢፌዴሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፤ “የግብጽ የውሃ ሐብት እና መስኖ ሚኒስትር ንግግር የሀገሪቱን ቆሞ ቀር የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ዳግም የሚያንጸባርቅ ነው” ያለው አዲስ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡
የሚኒስትሩ መግለጫ የመጣው የግብጽ የውሃ ሐብት እና መስኖ ሚኒስትር ሃኒ ሰዊይለም እሑድ እለት ለውጭ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ላይ ከአሸርቅ ብሉምበርግ ጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ኢትዮጵያ የራሷ በሆነው በዐባይ ወንዝ ላይ “ግድቦችን የመገንባት መብት ሙሉ ለሙሉ በሷ ብቻ የሚወሰን አይደለም” ሲሉ ከተናገሩ በኋላ ነው፡፡ ሃኒ ሰዊይለም በዚሁ ንግግር ወቅት “የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ስለዚህ ጉዳይ መማር አለባቸው” ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በጉዳዩ የተናገሩት የኢትዮጵያ የውሃ እና አነርጂ ሚኒስትር ሐብታሙ ኢተፋ፤ “አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ኢትዮጵያ የራሷ በሆነው የዐባይ ወንዝ ላይ ተጨማሪ ግድቦችን የመገንባት ሉዓላዊ መብት አላት” ሲሉ ገልጸው ነበር፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 12/2019 ባሰራጨው መግለጫ፤ የግብጹን ሚኒስትር ንግግር “እጅግ የሚያሳዝን ነው” ብሎታል፡፡ ይህ ንግግር “ግብጽ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት የምትከተለውን ኋላ ቀር የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ዳግም ያንጸባረቀ” መሆኑን በመግለጽ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ለግብጽ፤ የዐባይ ተፋሰስ ሀገራት የውሃ ሐብታቸውን ለማልማት “ፈቃዷን መጠየቅ ቅድመ ሁኔታ ይመስላታል” ያለው መግለጫው፤ “ይህ አስተሳሰብ፣ ተንኳሽ ንግግሮችም ሆነ በጉዳዩ ላይ የምታራምደው አቋም በመላው ተፋሰሱ ትብብር ማዕቀፍ ውስጥ” ቦታ እንደሌላው አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
“ኢትዮጵያ የአሁኑን እና የወደፊቱን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት” ዐባይ ወንዝን ጨምሮ የተፈጥሮ ሐብቷን የመጠቀም ሉዐላዊ መብቷን ዳግም ማረጋገጧን በማስታወስ፤ “ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ከሞኖፖሊያዊ ፉክክር እና ማግለል ይልቅ የትብብር፣ የጋራ ብልጽግና የክልል ውሕደትን ማንጸባረቅ” እንደሚኖርባቸው በመጥቀስ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የምታራምደውን አቋም በድጋሚ አንጸባርቋል፡፡
መግለጫው አክሎም ካይሮ ከቀድሞው “ቆሞ ቀር ፖሊሲ በመውጣት” ጉዳዩን “በጋራ መከባበር እና በረዥም ጊዜ የጋራ ጥቅሞች ላይ” ለተመሠረተው የ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የምትቀርብበት “ጊዜው አሁን” መሆኑን አስታውሷል፡፡ “ያረጁ የበላይነት ሕልሞችን በማስወገድ ከእውነታው ጋር መታረቅ” እንደሚገባም አስገንዝቧል፡፡
የግብፅ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የሚጠቅሱት የቅኝ ግዛት ስምምነት እ.አ.አ በ1959 የተፈረመና አብዛኛውን የውሃውን ድርሻ ለሀገሪቱ የሚሰጣት ነው፡፡ በዚህም የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻቸው ስለመጠቀም ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በየዓመቱ ከሚፈሰው 84 ቢሊዮን ኩየቢክ ውሃ 12 በመቶው በትነት የሚያልቅ ሲሆን፣ ይህ ስምምነት በዋነኝነት ግብጽን ትገዛ የነበረችውን ብሪታንያን ለጥጥ ምርቷ በዋነኝነት ተጠቃሚ አድርጓታል።
በኢትዮጵያ በኩል ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ እንድታገኝ እና 86 በመቶ የናይልን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይ እና ኢ ፍትሐዊ እንደሆነ ባለሥልጣናት በዓለም መድረክ ሲከራከሩ ቆይተዋል። (ሚንበር ቲቪ)












