- “በተለያዩ ሀገራት በሕግና በሃይማኖት የተከለከሉ ነገሮች የሚሠሩ ወጣቶች አሉ” – የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
- ማኅበረሰቡ አቀባበሉ ጤናማ አይደለም – የሥነ ልቡና ባለሞያ
ይፋዊ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱ በዓለማችን የተለያዩ አካባቢዎች አብዛኛዎቹ ሰዎች የሚፈልሱት በምርጫቸው ቢሆንም፣ ሌሎች ደግሞ በአስገዳጅ ሁኔታዎች ምክንያት ይሰደዳሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ (UNHCR) እንደዳስቀመጠው ግምት ከሆነ፣ እስከ በ2017 አጋማሽ ድረስ ዓለም 36 ነጥብ 9 ሚሊዮን ስደተኞችን አስተናግዳለች፡፡ ይህም በተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ረድኤትና ሥራ ኤጀንሲ (UNRWA) የኃላፊነት ማዕቀፍ ስር የሚገኙ 5 ነጥብ 9 ሚሊዮን የፍልስጤም ስደተኞችን፣ እንዲሁም 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ጥገኝነት ጠያቂዎችን ያካትታል። እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እና ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (ILO) ባሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች መረጃ መሠረት፤ ግጭት፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር እና የአየር ንብረት ለውጥ በየዓመቱ ከመቶ ሺሕ በላይ ሰዎች ከኢትዮጵያ እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡
ከ“ሚንበር ቲቪ” ጋር ቆይታ ያደረጉት በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ክትትልና ድጋፍ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደረጄ ተግይበሉ ምን አሉ?
“ዜጎች በመደበኛ እና መደበኛ ያልሆነ መንገድ ለፍልሰት ይነሳሉ፤ ቀዳሚው መንገድ በሕጋዊ መንገድ የሚደረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው በሰው አዘዋዋሪዎች እና ደላሎች አማካኝነት የሚደረገው “ሕገ ወጥ” የሚባለው ነው፡፡ በሁለቱም መንገድ ከተጓዙት መካከል ለተመላሾች መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ሂደት ያለፉ ወደ ሥራ እንዲገቡ ሲደረግ ዜጎች መልሰው የመሄድ አዝማሚያ ያሳያሉ፡፡ የአንዳንዶቹ ችግር በነበሩበት ሀገር በአነስተኛ የሥራ ዘርፍ ለምሣሌ ፍየል ጠብቀው የሚከፈላቸው ገንዘብ እዚህ ሊያገኙት ከሚችሉት ጋር ሲያነጻጽሩት አለመመጣጠን ያጋጥማልቸዋል፡፡
መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከሚፈልሱት ውስጥ በሀገራቱ መንግሥት በሕግና በሃይማኖት የተከለከሉ ነገሮች የሚሠሩ ወጣቶች አሉ፤ እነዚህም አልኮል መሸጥና መሣሪያ ማዘዋወርን ያካትታል፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ደግሞ በመደበኛ አሠራር የሚያገኙት ገቢ የማነጻጻር እና ለሀገር ውስጥ አማራጮች ብዙም ትኩረት ያለመስጠት ነገር በአንዳንድ ወጣቶች ላይ ይታያል፡፡ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከሀገር የወጡት እነዚህ ዜጎች የተለያዩ ዐይነት እንግልትና ጉዳት ሊያስተናግዱ ይችላሉ፡፡
ባለፉት 5 ዓመታት 94 በመቶ ገደማ ፍልሰተኞች የተነሱት ከአማራ፣ ከትግራይና ከኦሮሚያ ክልሎች ነው፡፡ ተመላሾቹ ዜጎች ተመልሰው ለመሄድ የሚያሳዩትን ስሜት ለማስቀረት በተለያዩ የምክርና የሥልጠና መድረኮች እንዲሁም ከተለያዩ የድንበር ተጋሪ አገራት ጋር በጋራ ለመከላከል እየተሠራ ይገኛል፡፡”

በዚህ ጉዳይ ላይ “ሚንበር ቲቪ” ያነጋገራቸው በሐርመኒ የሥነ ልቡና ማማከር ውስጥ የሚሠሩት የሥነ ልቡና ባለሞያው አቶ መሐመድ ሷሊህም እንዲሁ በሥራቸው ጠባይ ምክንያት ከስደት ተመላሽ ዜጎች ወደመጡበት ሀገር ተመልሰው የመሄድ ፍላጎንት በተደጋጋሚ እንደሚመለከቱ ገልጸዋል፡፡ “ከእነዚህ ሰዎች ጋር ስንሠራ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት የሚሰጣቸውን የመቋቋሚያ ገንዘብ መልሰው ለመሄድ እንደሚያውሉት እናስተውላለን፡፡ ተመላሾች ይህን የሚያደርጉት ተመልሰው ሲሄዱ የከፋ አደጋ ሊገጥማቸው እንደሚችል እያወቁ ነው፡፡ ነገር ግን ለዚህ እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው ማኅበረሰቡ ለተመላሾች መልካም አቀባበል አለማድረጉ ጭምር ነው”፡፡
የሥነ ልቡና ባለሞያው ከተመላሽ ዜጎችም ይጠበቃል ያሉትን ተናግረዋል፡፡

“አንደኛው ሕይወታቸውን ቆም ብለው ማሰብ ይኖርባቸዋል፤ ድጋፍ የሚሰጡ አካላትን መለየት ያስፈልጋል፤ እለት ተዕለት ኑሯቸውን ጤናማ ማድረግ እንዲሁ ይጠበቃል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንደኛው ተግዳሮት ከስደት ተመላሾች ሱስ ሊኖርባቸው ይችላል፤ ይህን መታከም ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም ሊያደርጉት የሚችሉት ትንሹ ነገር፤ አዋዋላቸውንና ጤናቸውን መጠበቅ ነው፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ሣምንት መስከረም 5/2019 ባሰራጨው መረጃ እንዳመለከተው፤ ልክ በ2018 መስከረም ወር በተጀመረው ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ሥራ እስካሁን 101 ሺሕ 800 በላይ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር መመለስ ተችሏል። (ሚንበር ቲቪ)












