Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችበእስልምና ቅዱሳን ሥፍራዎች ላይ ሥጋት የደቀነው ጦርነት

በእስልምና ቅዱሳን ሥፍራዎች ላይ ሥጋት የደቀነው ጦርነት

የእስልምና ቅዱሳን ሥፍራዎች የሚገኙባት ሳዑዲ ዐረቢያ ትላንት ማክሰኞ በድንገት ለዜጎች የአደጋ ጊዜ የደኅንነት ማስጠንቀቂያ መስጠቷ ድንጋጤን ፈጥሮ አልፏል፡፡ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት የደኅንነት ማስጠንቀቂያውን የሰጡት በዋነኝነት አንደኛውን ቅዱስ ሥፍራ ለያዘችው መካ ከተማ ነዋሪዎች ነበር፡፡ የጣኢፍ እና የሀገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ለሆነችው ጂዳ ነዋሪዎችም ማስጠንቀቂያው ደርሷቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ የደኅንነት ማስጠንቀቂያው መነሳቱ ተገልጾ ዜጎች ወደቀደመ እንቅስቃሴ ለመመለስ ችለዋል፡፡

ለአዋጁ ምክንያት ሆኗል የተባለው በይፋዊ መጠሪያው “አንሳሩላህ” የሚባለው የየመኑ ‘ሑውሲ’ ታጣቂ ቡድን የሰነዘረው ጥቃት ነው፡፡ ይህን ያሳወቀው ደግሞ በየመን ግጭት ውስጥ በመግባት ከአማጺያኑ ጋር የሚዋጋው በሳዑዲ የሚመራው የዐረብ ጥምረት ነው፡፡ የጥምረቱ ቃል አቀባይ ቱርኪ አልማሊኪ እንደተናገሩት፤ በሑውሲ የተቃጣውን የድሮን ጥቃት ጥምረቱ “መክቶታል”፡፡ ድርጊቱን በቅዱሳን ሥፍራዎች ላይ የሚገኙ “ምዕመናን ላይ ፍርሐት ለመንዛትና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የተደረገ ሙከራ” ነው በማለት የኮነኑት አልማሊኪ፤ በመካ የሚገኙ ምዕመናን ሊታለፉ የማይቻል “ቀይ መስመር” መሆናቸውን በመጠቅስ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡

በጥቃት አድራሽነት ሥማቸው የተጠቀሰው የአንሳሩላህ አማጺያን በበኩላቸው፤ ቅዱሳን ሥፍራዎችን የጥቃት ዒላማ አድርገዋል መባሉን አስተባብለዋል፡ የቡድኑ ተወካዮች ለየመኑ ሳባ የዜና አገልግሎት በሰጡት መግለጫ፤ በሌሎች የእስልምና ቅዱሳን ሥፍራዎች ላይ “ሥጋት ደቅነዋል” መባላቸውንም አጥብቀው በመከላከል መረጃውንም “አሳሳች” ነው በሚል ፈርጀውታል፡፡

በርግጥ ሳዑዲ ዐረቢያ የሑውሲ አማጺያን በተመሳሳይ ቅዱሳን ሥፍራዎች ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ በሚል የደኅንነት ማስጠንቀቂያ ስትሰጥ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም፡፡ ከዘጠኝ ዐመት በፊት በይዘቱ የሚመሳሰል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ነበር፡፡

በሑውሲ እና በሳዑዲ ዐረቢያ በሚመራው ጥምር ኃይል መካከል የሚካሄደው ጦርነትና የሳዑዲ ጣልቃ ገብነት በይፋ የተጀመረው በመጋቢት 2007 ነው፡፡ ጉዳዩን የሚከታተሉ ተንታኞች ይህ ጦርነት የተጀመረበት ዋና ምክንያት ነው የሚሉት፤ ሑውሲዎች የየመን ዋና ከተማ ሰንዓን በመቆጣጠር ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውን የሀገሪቱን መንግሥት ከሥልጣን ማውረዳቸውን ተከትሎ፣ ሳዑዲ ዐረቢያ የተባረረው መንግሥት እንደገና ወደ ሥልጣን እንዲመለስ እና የሑውሲዎችን መስፋፋት ለመግታት በማሰብ ጥምር ጦር አስተባብራ በየመን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ስትጀምር ነው፡፡  

ግጭቱ ሲባባስ በ2014 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት የተካሄደው የተኩስ አቁም ድርድር በሳዑዲ ግዛት የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በአብዛኛው የገታ ቢሆንም፤ የሑውሲ አማጺያን በሳዑዲ መርከቦች ላይ እገዳ መጣላቸውን በማወጅ በሀገሪቱ የባብ አል መንደብ ዳርቻ ላይ ወሳኝ የሚባሉ ቦታዎችን ከተቆጣጠሩ ወዲህ ግጭቱ እንደገና ተባብሷል፡፡ በኢራን የተለያየ እገዛ ይደረግለታል የሚባለው ቡድኑ በቅርቡ በሳዑዲ ዐረቢያ ላይ ሚሳዔሎችንና ድሮችኖችን አስወንጭፏል፡፡ ሪያድ በበኩሏ ቡድኑ በቅርብ ባስወነጨፋቸው በእነዚህ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎችና የኢኮኖሚ ተቋማትን ዒላማ አድርጓል በሚል ክስ ታቀርባለች፡፡

በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት ማክሰኞ እለት በሰጠው መግለጫው፤ ቡድኑ የሳዑዲ ከተሞች በሆኑት ኸሚስ ሙሸይጥ፣ አብሃ እና ጣኢፍ ከተሞች ጥቃት በመሰንዘር 13 ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን በመጥቀስ፤ ለጥቃቱ ብርቱ ምላሽ እንደሚሰጥ ዛቻ ሰንዝሯል፡፡  

እ.አ.አ በ1990ዎቹ የተመሠረተው “ሑውሲ” ሥሙን የወረሰው ከቀድሞ መሥራቹ ሑሴን አን ሑውሲ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የሚመራው በወንድምዬው ዓብዱልማሊክ ሑውሲ ነው፡፡ በ2000ዎቹ መጀመርያ ላይ በሰሜናዊ የመን ክልል ውስጥ ሰፊ የራስ ገዝ አስተዳደርን በመጠየቅ ከቀድሞው የየመን ፕሬዝዳንት ዓሊ ዐብደላህ ሳሊህ መንግሥት ጋር ተከታታይ ጦርነቶችን አድርጓል፡፡

በ2011 የዐረብ አብዮት ወቅት፣ ፕሬዝዳንቱ ሳሊህ ሥልጣኑን ለምክትላቸው ለዓብዱልረብ መንሱር ሐዲ ለማስረከብ ተገደዱ፡፡ ሆኖም የመንሱር መንግሥት ችግር ውስጥ በመግባቱ ከሳሊህ እና ከታማኝ የጸጥታ ኃይሎች ጋር ያልተጠበቀ ጥምረት ከመሠረቱ በኋላ፣ የየመንን ዋና ከተማ ሰንዓን ከመቆጣጠራቸው በፊት የሰሜናዊቷን የሰዓዳን ግዛት በቁጥጥራቸው ስር አውለው ሐዲ ሀገር ለቅቀው ወደ ውጭ እንዲሸሹ ተገደዱ፡፡ ከየመን ጋር የምትጎራበተው ሳዑዲ ዐረቢያ ሑውሲዎች የመንን በመቆጣጠር “ሜዳውን የኢራን መጫወቻ ሊያደርጉት ነው” በሚል የዐረብ ጥምረት በመፍጠር ወደ ጦርነት የገባችው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular