የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ)፤ እ.ኤ.አ. በ2025 በዓለም ዙሪያ ከቅድመ-አንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ የሚገኙ ከ171 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወይም ከ10 ተማሪዎች አንዱ በአየር ንብረት አደጋዎች ምክንያት ትምህርታቸው መስተጓጎሉን አስታውቋል።
ጉዳቱ ከደረሰባቸው 171 ሚሊዮን ተማሪዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት የሚኖሩ ናቸው። ኢትዮጵያም በአየር ንብረት አደጋ ትምህርት ከተቋረጠባቸው ሀገራት መካከል እንደሆነች በሪፖርቱ ተካታለች።
“Learning Interrupted: Global Snapshot of Climate-Related School Disruptions in 2025” በሚል ርእስ የወጣው የድርጅቱ ሪፖርት፤ የ106 ሀገራትን እና ግዛቶችን መረጃ የዳሰሰ ነው። በዚህም እንደ አውሎ ነፋስ፣ ጎርፍ፣ የሙቀት ማዕበል፣ ድርቅ እና የሰደድ እሳት ያሉ የአየር ንብረት አደጋዎች ትምህርት እንዲቋረጡ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲወድሙ እና የመማሪያ ጊዜያት እንዲያጥሩ ምክንያት መሆናቸው ተብራርቷል።
እንደ ዩኒሴፍ መረጃ ከሆነ አውሎ ነፋስ ባለፈው አንድ ዓመት ለትምህርት መስተጓጎል ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ 109 ሚሊዮን ተማሪዎችን ከትምህርት በማስተጓጎል በቀዳሚነት ተጠቅሷል። እንዲሁም የጎርፍ አደጋ ቢያንስ 70 ሚሊዮን ያህሉን ከትምህርት ገበታ አፈናቅሏል። የሙቀት ማዕበልም በተመሳሳይ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሕጻናት ትምህርት መቋረጥ ምክንያት ሆኗል፡፡
ትምህርታቸው ከተስተጓጎለባቸው ተማሪዎች መካከል 66 በመቶ የሚሆኑት ትምህርታቸው ሙሉ በሙሉ የተቋረጠ ሲሆን፣ 21 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ደግሞ ትምህርት ቤቶቻቸው በመውደማቸው አልያም ለተፈናቃዮች ጊዜያዊ መጠለያነት በመቀየራቸው ትምህርት መጀመር አልቻሉም፡፡
የተከሰተው የትምህርት መቋረጥ የተማሪዎችን የእውቀት እድገት በመግታት እና የትምህርት እኩልነት ክፍተትን በማስፋት ቢያንስ 200 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አሳጥቷቸዋል፡፡
ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ሀገራት መካከል ፓኪስታን በቀዳሚነት ተጠቅሳለች፡፡ በነሐሴ ወር በተከሰተው የከባድ እና መካከለኛ ዝናብ ጎርፍ ከ28 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ሳይመለሱ ቆይተዋል ተብሏል።
የዩኒሴፍ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካትሪን ራስል “የአየር ንብረት አደጋዎች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሕፃናት ትምህርት ከማስተጓጎል ባለፈ ትምህርት ቤቶችን በማውደም እና ቤተሰቦችን በማፈናቀል ተጋላጭ የሆኑ ሕፃናትን ከትምህርት ገበታ እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል” ብለዋል። አክለውም “የዛሬ እና የነገ ሕፃናትን ትምህርት ለመጠበቅ የአየር ንብረት አደጋዎችን መቋቋም በሚችሉ ትምህርት ቤቶች እና የትምህርት ሥርዓቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለብን” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። (ሚንበር ቲቪ)












