Homeነፃ ሀሳብ“የቢሊዮን ብር ጥያቄ፡ ኢንሹራንስ ከእስልምና ጋር ይጣጣማል?”

“የቢሊዮን ብር ጥያቄ፡ ኢንሹራንስ ከእስልምና ጋር ይጣጣማል?”

ፕሮፊሰር አና ቲባይጁካ በታንዛኒያ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ሥም ያላቸው አንጋፋ ግለሰብ ናቸው። በናይሮቢ የነበረው የተባበሩት መንግሥታት የሰፈራ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር በመሆን ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል። በዚህ ኃላፊነታቸው በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ከፍተኛውን ሥልጣን ከያዙ ጥቂት አፍሪካውያን ሴቶች አንዷ ነበሩ። ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ በታንዛኒያ ካቢኔ ውስጥ የኢኮኖሚ፣የመሬት፣ የቤት እና የሠፈራ ልማት ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።

ፕሮፌሰሯ በዛሬው እለት በታንዛንያው ሲቲዝን ገጽ ላይ “የቢሊዮን ሽልንግ ጥያቄ፡ ኢንሹራንስ ከእስልምና ጋር ይጣጣማል?” የሚል ርእስ ያለው መጣጥፍ አስነብበዋል፡፡ መነሻ የሆናቸው በዚህ ሣምንት አንድ የእስልምና ሃይማኖት መምሕር “ኺድማ ኦንላይን ቲቪ” በተሰኘ መገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርበው የጤና ኢንሹራንስ ከቁማር ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ “ሐራም ነው” የሚል አስተያየት መስጠታቸው ነው፡፡ መምሕሩ በንግግራቸው ሙስሊሞች ከኢንሹራንስ ተቆጥበው በምትኩ “ለአገልግሎቶች ቀጥታ ክፍያ እንዲፈጽሙ” አሳስበዋል። ይህ ንግግር በታንዛኒያ ማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ከፍተኛ ክርክር ቀስቅሷል።

ይህ የመምሕሩ አቋም የተንጸባረቀው የሀገሪቱ መንግሥት ለሁሉም ዜጎች ሁለንተናዊ የጤና ኢንሹራንስን እያስተዋወቀ ባለበት ወቅት ነው። በሀገሪቱ በአሁኑ ጊዜ በ2022 በወጣው የተካፉል መመሪያ መሠረት ፈርስት ዩናይትድ ተካፉል እና ሲ.አር.ዲ.ቢ ባንክ ባሉ ተቋማት አማካኝነት እየቀረበ ይገኛል። አገልግሎቶቹ የሚሰጡት በንብረትና ሐብት እንዲሁም የቤተሰብ (የሕይወት) ዋስትና ነው፡፡

ታንዛንያ ይህን ባስተናገደችበት ሣምንት በኢትዮጵያ ደግሞ ማዕከላዊው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ በሀገሪቱ በመስኮት ደረጃ ሲሰጥ የነበረውን የእስላማዊ ኢንሹራንስ አገልግሎት በተሟላ መልኩ እንዲሰጥ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቷል፡፡

አዋጁ በዋናነት በ“መስኮት” ደረጃ ሲሰጥ የነበረው አገልግሎት በአዲሱ አዋጅ ሙሉ ለሙሉ እንዲሰጥ ፍቃድ ከማስገኘቱ ባለፈ አስተዳደር ላይ ለውጥ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ በቀደመው አዋጅ አስተዳደር በቦርድ ቁጥጥር ይደረግበት ነበር፡፡ አዲሱ አዋጅ ይህን በመሻር “የልዩ የብቃት ምዘና እና የሸሪዓ ኮሚቴ” እንዲቋቋም ያስገድዳል፡፡

አዋጁ ሲጸድቅ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ቁጥጥር ባለሥልጣን “የተካፉል፣ የመስኮት ተካፉል እና የውጭ ተካፉል ኦፕሬተሮችን” የፈቃድ አሰጣጥ መስፈርቶችን በመመርያ ይወሰናል፡፡ ይህ አዋጅ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለሥልጣኑ የተካፉል ኢንሹራንስ ከተለመደው ኢንሹራንስ “ካለው የተለየ ባሕርይና የአሠራር ዘይቤ አንጻር” ለቁጥጥርና ለፈቃድ አሰጣጥ የሚያስፈልጉ ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታዎችን በመመሪያ ያወጣል፡፡ ይህን ተከትሎ የማዕከላዊውን ባንክ ይለፍ ወረቀት ለማግኘት ወረፋ የያዘው በኢትዮጵያ የመጀመርያው ወለድ አልባ የኢንሹራንስ አገልግሎት ሰጪ “አማና ኢንሹራንስ” ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 83 ባለድርሻዎችን ያቀፈው አዲስ መጪው ኩባንያ፤ በባለድርሻነት በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ከሚሰጡ አራት ባንኮች መካከል፤ ሂጅራ፣ ራሚስ እና ሸበሌ አካቷል፡፡

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ፈቃድ ሊያገኝ ከጫፍ የደረሰው ተካፉል እስካሁን ድረስ በመስኮት ደረጃ ሲሰጥ የቆየ ነው፡፡ “ተካፉል” እንደ ተለምዷዊው የኢንሹራንስ ዐይነት አይደለም፡፡ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ተሳታፊዎች እርስ በርሳቸው ለመረዳዳት መዋጮ ይሰበስባሉ፡፡ መዋጮው የሚሰበሰበው ወደ ጋራ ፈንድ ነው፡፡ የካሣ ክፍያዎችም ወጪ የሚደረጉትም ከዚህ የጋራ ፈንድ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ትርፍ (Surplus) ካለ ለአባላቱ ይከፋፈላል ወይም እንዲጠራቀም በፈንዱ ይቀመጣል።

ሆኖም ከላይ የጠቀስናቸው የታንዛንያ ፕሮፊሰር እንደሚሉት አንዳንድ ጥያቄዎች በቂ ማብራሪያ የላቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት በሀገራቸው እንደተከሰተው አወዛጋቢ ብይኖች ወደ ኢትዮጵያም ሊመጡ የማይችሉበት ዕድል የለም፡፡ አንዳንድ የእስልምና ሊቃውንት አሠራሩን የሚጻረሩት በተለምዷዊው ኢንሹራንስ ውስጥ ያሉ በሸሪዓ የተከለከሉ የሚሏቸውን ሦስት ጉዳዮች ማለትም ርግጠኛ አለመሆን (ገራር)፣ ቁማር (መይሲር) እና ወለድ (ሪባ) ሊኖሩት ይችላል በሚል ነው፡፡ ለዚህ አስረጂ ተደርጎ የሚቀርበው መከራከሪያ፤ አንድ ሰው ፕሪሚየም ሲከፍል ምንም ዓይነት አገልግሎት ላይመለስለት ይችላል የሚለው ነው፡፡ መድን ሰጪው መቼ ክፍያ እንደሚፈጽም አያውቅም የሚለውንም ደርበው ያነሳሉ። አንደኛው ወገን ካዋጣው በላይ ሊያገኝ ስለሚችል፣ ሌላኛው ደግሞ ምንም ላያገኝ ስለሚችል ኢንሹራንስ ቁማርን ይመስላል የሚሉም አሉ፡፡

ከእነዚህ ውጪ ባለሞያዋም እንደጠቀሱት ደግሞ በዘርፉ በተደጋጋሚ የሚጠየቀው “የካሣ መጠን ካለው ፈንድ በላይ ቢሆን ምን ይከሰታል?” የሚለውም ሌላኛው አከራካሪ ጉዳይ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ እንዳሉት በተለመደው ኢንሹራንስ ውስጥ ይህ ችግር “ሪ ኢንሹራንስ” በመባል በሚጠራው አሠራር የሚፈታ ነው፡፡ በዚህ አሠራር አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ከደንበኞቹ የሚሰበስበው አደጋ በጣም ትልቅ ሲሆን፤ ስጋት ለመቀነስ የኢንሹራንስ ኩባንያው የገባውን ውል በከፊል ለሌላ ትልቅ ኩባንያ ያስተላልፋል። ይህን የሚያደርገው የኢንሹራንስ ኩባንያው ከደንበኛው ከሰበሰበው ክፍያ ላይ የተወሰነውን ለሪ-ኢንሹራንስ ኩባንያው በመክፈል ነው፡፡

በተካፉል ውስጥ ይህ ተግዳሮት አሁንም አስቸጋሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በርግጥ ሁሉም የእስልምና ሊቃውንት ኢንሹራንስን የተከለከለ አድርገው አይመለከቱትም፡፡ አንዳንዶች ኢንሹራንስ ቁማር ሳይሆን የአደጋ ሥጋት አስተዳደር ዘዴ ነው ይላሉ፡፡ ግለሰቦችን፣ ቤተሰቦችን እና ንግዶችን በመጠበቅ ለሕዝብ ጥቅም ግልጋሎት የሚውል ነው ይላሉ፡፡ ይህ አመለካከት በበርካታ የሙስሊም ሀገሮች ተቀባይነት በማግኘቱ እየተተገበረ እንደሚገኝ ፕሮፊሰር አና ቲባይጁካ ይገልጻሉ፡፡ በኢትዮጵያም የአገልግሎቱ በር እየተከፈተ በመሆኑ አደናጋሪዎቹ ብይኖች ከመምጣታቸው በፊት ሊቃውንት በርእሰ ጉዳዩ ላይ መነጋገሪያው ጊዜ አሁን ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ ቀጣዩ የቢሊዮን ብር ጥያቄ፦ “ኢንሹራንስ ከእስልምና ጋር ይጣጣማል?” የሚለው ይሆናል፡፡

ይህ ጽሑፍ በአስተያየት አምድ የተስተናገደ በመሆኑ የሚንበር ቲቪን አቋም አይወክልም፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular