የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ በኢትዮጵያ በመስኮት ደረጃ ሲሰጥ የነበረውን የእስላማዊ ኢንሹራንስ (ተካፉል) አገልግሎት በተሟላ መልኩ እንዲሰጥ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቷል፡፡ የባንኩ ገዥ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ወደ ኃላፊነት ከመጡ ወዲህ ተዘጋጅቷል የተባለው ረቂቅ አዋጅ፤ ዘርፉን ለማዘመን፣ የፋይናንስ መረጋጋትን ለማጠናከር እና የኢትዮጵያን የቁጥጥር ሥርዓት ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር ለማጣጣም የተነደፉ ሰፋ ያሉ ማሻሻያዎችን ያካተተ ነው፡፡
በ160 ገጾች የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በ16ኛው ክፍል ላይ ሸሪዐን መሠረት ያደረገ የኢንሹራንስ አገልግሎት ማለትም “ተካፉል”ን የተመለከቱ ጉዳዮችን አስፍሯል፡፡ በዋናነት በ”መስኮት” ደረጃ ሲሰጥ የነበረው አገልግሎት በአዲሱ አዋጅ ሙሉ ለሙሉ እንዲሰጥ ፍቃድ ከማስገኘቱ በተጨማሪ አስተዳደሩንም የሚለውጥ ነው፡፡ የቀደመው አዋጅ አስተዳደር በቦርድ ቁጥጥር ይደረግበት የነበረ ሲሆን፤ በአዲስ አዋጅ “የልዩ የብቃት ምዘና እና የሸሪዓ ኮሚቴ” መስፈርት ተቀምጧል፡፡
አዋጁ ሲጸድቅ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ቁጥጥር ባለሥልጣን “የተካፉል፣ የተካፉል መስኮት እና የውጭ ተካፉል ኦፕሬተሮችን” የፈቃድ አሰጣጥ መስፈርቶችን በመመሪያ እንደሚወስንም ተደንግጓል፡፡ ይህ አዋጅ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባለሥልጣኑ የተካፉል ኢንሹራንስ ከተለመደው ኢንሹራንስ “ካለው የተለየ ባሕርይና የአሠራር ዘይቤ አንጻር” ለቁጥጥርና ለፈቃድ አሰጣጥ የሚያስፈልጉ ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታዎችን በመመሪያ ያወጣል በሚል ደንግጓል፡፡
ባለሥልጣኑ አጠቃላይ የሸሪዓ አስተዳደር ሥርዓትን ለመቆጣጠር፤ ለፈቃድ አሰጣጥ የሚያስፈልጉ መስፈርቶች፤ የተካፉል መስኮት የሕግና የፋይናንስ ከለላ መስፈርቶች፤ የባለአክሲዮኖች፣ የተበሩዕ (የጋራ መረዳጃ መዋጮ) እና የኢንቨስትመንት ፈንዶች አያያዝ እና ክፍፍል እንዲሁም ለኦፕሬተሮች የሚፈለግ የካፒታል እና የብድር መክፈል አቅም መጠን በመመርያ የሚወስናቸው ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል ተካተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመርያው ወለድ አልባ የኢንሹራንስ አገልግሎት ሰጪ አማና ኢንሹራንስ ሥራ ለመጀመር የብሔራዊ ባንክን ፍቃድ እየጠበቀ እንደሚገኝ ከዚህ ቀደም አስታውቋል፡፡ ሥራ ለመጀመር የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛል የተባለው ኩባንያው 83 ባለድርሻዎችን ያቀፈ ነው። ከባለድርሻዎቹ መካከል በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ከሚሰጡ አራት ባንኮች ውስጥ ሦስቱ ይገኙበታል። እነዚህ ባንኮች ሂጅራ፣ ራሚስ እና ሸበሌ ናቸው። ባንኮቹ ያላቸው የድርሻ መጠን 5 በመቶ ነው። (ሚንበር ቲቪ)












