Homeዜናና ወቅታዊዜናበአሜሪካ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሙስሊም ሴቶች የሒጃብ መብት እንዲከበር ፍርድ ተላለፈ

በአሜሪካ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሙስሊም ሴቶች የሒጃብ መብት እንዲከበር ፍርድ ተላለፈ

የአሜሪካው የሙስሊሞች መብቶች ተቆርቋሪ ዘ ካውንስል ኦን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ የሚኒሶታ ቅርንጫፍ፤ በፌዴራል ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ሙስሊም ሴቶች ሒጃባቸውን የመልበስ መብታቸውን የሚያረጋግጥ ውሳኔ አሸንፏል፡፡ ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ ያለ ሒጃብ የተነሱ ፎቶግራፎች እንዲጠፉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የፍርድ ቤት ትዕዛዙ የተላለፈው በአሜሪካ የዲስትሪክት ፍርድ ቤት ዳኛ ጄፍሪ ኤም ብራያን አማካኝነት ነው፡፡ በዚህ ትዕዛዝ መሠረት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ቢሮ የሙስሊም ሴቶችን ሃይማኖታዊ መብት እንዲያከብርና የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዲጠብቅ ይገደዳሉ፡፡

ለውሳኔው መነሻ የሆነው ክስ የቀረበው በሚኒሶታ ማረሚያ ቤት በነበሩት ሶማሊያዊ አሜሪካዊት ሙና ጃማ ሥም ነው። እኒህ ወይዘሮ በማረሚያ ቤቱ ቆይታቸው ወቅት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ቢሮ ሒጃባቸውን አውልቀው ካልሆነ በስተቀር የመታወቂያ ፎቶግራፍ እንደማይነሱ በማሳወቁ በተደጋጋሚ በግዳጅ የተባሉትን አድርገዋል፡፡

ፖሊስ ያለ ሒጃብ የተነሱበትን ፎቶ የያዘ መታወቂያ እንዲይዙ በማድረግ፣ ወንድ የጥበቃ ኃይሎች በየቀኑ ፀጉራቸውን፣ ጆሯቸውን እና አንገታቸውን እንዲያዩ በማድረግ ለከፍተኛ ሥነ ልቦናዊና ሃይማኖታዊ ጫና ዳርጓቸዋል።

ዳኛ ብራያን በሰጡት ብይን የመንግሥት ርምጃ “የሃይማኖት ነፃነት መልሶ ማቋቋሚያ ሕግን” መጣሱን ገልጸዋል። መንግሥት አንድን ግለሰብ ከሃይማኖታዊ እምነቱ ውጪ እንዲያደርግ የሚያስገድድ ከሆነና ባለመታዘዙ ምክንያት ቅጣት እና ጥቅማጥቅሞችን የሚከለክል ከሆነ በሃይማኖት ነፃነት ላይ “ከፍተኛ ጫና” እንደፈጠረ ይቆጠራል ሲሉ የሕግ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ቢሮ ወይዘሮ ጃማ ያለ ሒጃብ የተነሱባቸውን ፎቶዎች በሙሉ በዘላቂነት እንዲደመስስ ተፈርዶበታል። ማረሚያ ቤቶችም የደኅንነት ሥጋትን እንደ ምክንያት በማቅረብ ብቻ የዜጎችን እምነትና ክብር መጣስ እንደማይችሉ በውሳኔው መረጋገጡን የመብት ተቆርቋሪው አስታውቋል፡፡

ውሳኔውን በተመለከተ የተናገሩት ወይዘሮ ሙና ጃማ፤ “ውሳኔው ትልቅ እፎይታ [የሚሰጥ] ነው፤ ሕገ መንግሥቱን እና መብታችንን የሚያከብሩ አካላት መኖራቸውን ማየቴ ለኔ ትልቅ ነገር ነው። አሁን በነፃነት መተንፈስ እንደምችል ይሰማኛል” ሲሉ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ የዘ ካውንስል ኦን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ የሕግ ባለሞያ አያ ቤይዱን በበኩላቸው፣ ውሳኔው በመላው አሜሪካ ለሚገኙ ሙስሊም ሴቶች ትልቅ ድል መሆኑን በመግለጽ፤ በማንኛውም የሕግ ተቋም ውስጥ “የግለሰቦች ሰብዓዊ ክብር እና ሃይማኖታዊ ተግባር” ያለ በቂ ምክንያት መጣስ እንደሌለበት አሳስበዋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular