Homeዜናና ወቅታዊዜናጀርመን “በአውሮፓ የመጀመርያውን” የእስልምና ሥነ መለኮት ፋኩልቲ ማቋቋሟን ይፋ አደረገች

ጀርመን “በአውሮፓ የመጀመርያውን” የእስልምና ሥነ መለኮት ፋኩልቲ ማቋቋሟን ይፋ አደረገች

በጀርመን የሚገኘው የሙንስተር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ያለውን የእስልምና ሥነ-መለኮት ማዕከል በአካዳሚክ መዋቅሩ ውስጥ ሙሉ ዕውቅና ወዳለው ፋኩልቲነት ቀይሮታል። እንደ ጀርመን መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ከሆነ፣ ፋኩልቲው በጀርመን ውስጥ በዐይነቱ የመጀመርያው ነው፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲው ገለጻ ደግሞ በአውሮፓም የመጀመሪያው ይሆናል።

ከሙከራ ፕሮጀክትነት ወደ ቋሚ መዋቅር የተለወጠው የአሁኑ የእስልምና ሥነ መለኮት ማዕከል፤ የተቋቋመው እ.አ.አ በ2012 ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ወደ ፋኩልቲነት እንዲያሳድገው ምክንያት ሆኖታል የተባለው፤ በአሥር ዓመታት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን እና በርካታ ባልደረቦች ማፍራቱ ነው፡፡ በዚህ ለውጥ ፋኩልቲ የዶክትሬት ዲግሪ መስጠት፣ የፕሮፌሰሮች ምርጫ ላይ መሳተፍ እና የራሱን የትምህርት ዕቅድ መንደፍ ይችላል፡፡ ይህም ከሌሎች ቤተ እምነት ፋኩልቲዎች ጋር እኩል ደረጃ ላይ ያስቀምጠዋል ተብሏል።

የሙንስተር ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም የእስልምና ሥነ መለኮት ማዕከሉን ያቀፈው በፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ ለትምህርት ቤቶች የሚሆኑ የሃይማኖት መምህራንም እዚሁ ይሠለጥኑ ነበር። በአዲሱ አወቃቀር የእስልምና ሥነ መለኮት አሁን የራሱን የዶክትሬት ዲግሪ ከመስጠት መብት ባሻገር የፈተና ኮሚሽኖችን ራሱን ችሎ የመሠየም ዕድል ያገኛል።

የፋኩልቲው መሥራች ዲን ሙሐነድ ኾርሺድ እንደገለጹት፣ ርምጃው ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡ “ይህ ለሙስሊሞች የዕውቅና ምልክት ነው” ሲሉም ተድምጠዋል፡፡  

ፋኩልቲው ሥራ እንዲጀምር የእስልምና ታሪክን፣ ግብረ ገብን እና ፍልስፍናን ጨምሮ የስምንት ፕሮፌሰርነት የሥራ መደቦች የገንዘብ ድጋፍ በሰሜን ራይን ዌስትፋሊያ ግዛት ተገኝጧል ተብሏል። አዲሱ ፋኩልቲ በአሁኑ ወቅት ግንባታው እየተከናወነ በሚገኝ አዲስ የሥነ መለኮት ግቢ ካምፓስ ውስጥ የሚገኝ ነው። የፋኩልቲው የእስልምና መምሕራንም በሙንስተር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ካሉ እንደ ካቶሊክ እና ፕሮቴስታንት ካሉ ሌሎች የሃይማኖት መምሕራን ባልደረቦሽ ጋር የጋራ ቤተ መጽሐፍት እና ካፌቴሪያ የሚጠቀሙ ይሆናል።

በጀርመን የሚገኘው የሙንስተር ዩኒቨርሲቲ የእስልምና ሥነ መለኮት ፋኩልቲ ሥራውን ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው በሰኔ ወር መገባደጃ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular