Homeዜናና ወቅታዊዜናበናይጄሪያ የዘንድሮውን የሐጅ ጉዞ ለመታደግ ባለድርሻ አካላት የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት ጠይቀዋል

በናይጄሪያ የዘንድሮውን የሐጅ ጉዞ ለመታደግ ባለድርሻ አካላት የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት ጠይቀዋል

በናይጄሪያ የአቪዬሽን ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት፣ በዘንድሮው የሐጅ ጉዞ የሀገሪቱን ምዕመናን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በሰላም የመጓጓዝ ሂደት እየተፈታተነ ያለውን የአቪዬሽን ነዳጅ ዋጋ ንረት ለመቅረፍ፤ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በአፋጣኝ ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ጥሪውን ያቀረቡት “የአቪዬሽን ባለድርሻ አካላት” በሚል ሥያሜ የተደራጁ አካላት ናቸው፡፡ ቡድኑ እየጨመረ የመጣው “የነዳጅ ዋጋ ያስከተለውን ከባድ የሎጂስቲክስ እና የፋይናንስ ፈተና ለመቋቋም” እንዲሁም የዘንድሮውን የሐጅ ጉዞ ክንውን ለመታደግ አፋጣኝ ርምጃ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል፡፡

የቡድኑ ፕሬዝዳንት አልሐጂ ቡካልቲ ዑስማን ጋማዋ እሑድ ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ የአቪዬሽን ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር በሺሕዎች የሚቆጠሩ ናይጄሪያውያን ምዕመናን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚያደርጉት የአየር ጉዞ ሥጋት ላይ መጣሉን ቀጥሏል ብለዋል። የሐጅ ጉዞ ውል የገቡ በርካታ አየር መንገዶች የፍላጎት መጠኑን ለማሟላት አውሮፕላኖችን በኪራይ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። አሁን ባለው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት፣ አየር መንገዶቹ ያቀዱት የነበረው የትርፍ ሕዳግ ሙሉ በሙሉ ተሟጧል ሲሉም አክለዋል፡፡

በአንዳንድ ሁኔታዎች አየር መንገዶቹ የኪራይ እና የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ከሸፈኑ በኋላ ምንም ትርፍ ሳያገኙ “በነፃ” እንደመብረር ሊሆንባቸው ይችላል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ አስቸኳይ ርምጃ ካልተወሰደ አንዳንድ አየር መንገዶች “ከናይጄሪያ ጉዞ ለመጀመርም ሆነ ከሳዑዲ ዓረቢያ የመልስ ጉዞዎችን ለማድረግ” የገንዘብ አቅማቸው ሊፈቅድላቸው አይችልም ሲሉ አስረድተዋል።

የቡድኑ ፕሬዝዳንት የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ለሐጅ ጉዞዎች ቀጥተኛ ድጎማ ባያደርጉ እንኳ የጉዞው ሂደት እንዳይደናቀፍ አፋጣኝ የፖሊሲ ርምጃዎች፣ የዋጋ ቁጥጥር፣ የውጭ ምንዛሬ ድጋፍ ወይም ስልታዊ የነዳጅ አቅርቦት ዝግጅቶችን እንዲያደረጉ ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡  

ጋማዋ እንደገለጹት ከመንግሥት፣ ከተቆጣጣሪ አካላት፣ ከአየር መንገዶች እና ከነዳጅ አቅራቢዎች ፈጣን ጣልቃ በመግባት በቅንጅት ካልተሠራ፤ የዘንድሮ የሐጅ ጉዞ በታሪክ ከፍተኛው የዋጋ ጭማሪ ሊታይበት ይችላል፡፡ ከዚህ የሚከፋ ከሆነ ከሆነ ደግሞ ሥራው ሙሉ በሙሉ ሊስተጓጎል ይችላል። በናይጄሪያ የሐጅ ውሎች በተፈረሙበት ወቅት አንድ ሊትር ነዳጅ 1 ሺሕ ናይራ አካባቢ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዐት ዋጋው ስ ሺሕ ናይራ ደርሷል፡፡ በዚህ ወቅት በሳዑዲ በኩል አንድ ሊትር ነዳጅ 0.68 ዶላር ገደማ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ 1 ነጥብ 40 ዶላር አካባቢ ከፍ ማለቱ ተገልጿል። ይህም በዶላር ሲሰላ ከ105 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል። ናይጄሪያ ለሐጅ ሥነ ሥርዓት 67 ሺሕ ገደማ ምዕመናንን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ትልካለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሥነ ሥርዐቱ ላይ ለመሳተፍ ከኢትዮጵያ ከአምስት ሺሕ በላይ ምዕመናን መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሐጅና ዑምራ ዘርፍ ከዚህ ቀደም አሳውቋል፡፡ የዘርፉ ኃላፊ ሐጅ ዓብዱልፈታህ ሙሐመድ ለ“ሚንበር ቲቪ” እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ሰዐት በተፈጠረው በመካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋት ሳቢያ የሐጅ ተመን ላይ ጭማሪ አይኖርም፡፡ ኃላፊው፤ “በዋጋ ተመኑ ላይ ሑጃጁ ተመዝግበው ሳዑዲ ደርሶ እስኪመለሱ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሊኖር የሚችለው የገበያ ሁኔታና ሊከሰት የሚችል የምንዛሬ ልዩነት ከግምት ገብቷል” ብለዋል፡፡ “ከዚህ አኳያ ሑጃጁ ደርሰው እስኪመለሱ ድረስ ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ አይኖርም ብለን እንጠብቃለን” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular