Homeዜናና ወቅታዊዜናከሸበሌ ባንክ ካፒታል ውስጥ እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ለማድረግ...

ከሸበሌ ባንክ ካፒታል ውስጥ እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ለማድረግ በክልሉ ካቢኔ ዝግጁነት መኖሩን ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ ገለጹ

የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ካቢኔ፤ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ አገልግሎት ከሚሰጠው ከሸበሌ ባንክ ካፒታል ውስጥ እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ለማድረግ “ፍላጎቱም ሆነ ዝግጁነቱ” እንዳለው የባንኩ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ አቶ ዓብዱልመጂድ ሙሐመድ ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል የሶማሌ ማይክሮ ፋይናንስ በመባል ይጠራ የነበረው ሸበሌ ባንክ፤ ሸሪዓን ያሟላ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ አገልግሎት ወደመስጠት የተሸጋገረው በ2013 ነው፡፡ ባንኩ ድርሻውን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት የማድረጉ የካቢኔ ውሳኔ በ2017 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀውን የውጭ ባንኮች የኢትዮጵያን ባንክ ዘርፍ እንዲቀላቀሉ የሚፈቅደውን አዋጅ መሠረት በማድረግ የሚከናወን ነው፡፡

አዋጁ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ቅርንጫፎችን ወይም የውክልና ቢሮዎችን በመክፈት ወይም ነባር ባንኮችን አክሲዮን በመግዛት ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ ያስችላቸዋል። የውጭ ሀገር ስትራቴጂካዊ ባለሐብቶችን ባለቤትነት ግን በየትኛውም የኢትዮጵያ ባንክ ውስጥ በ40 በመቶ ይገድባል፡፡ ስትራቴጂካዊ ያልሆኑ የውጭ ባለሀብቶች ደግሞ ተጨማሪ ከ7 በመቶ እስከ 10 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ እንዲኖራቸው ይፈቅዳል።

በተጨማሪም አዋጁ በኢትዮጵያ ባንክ ውስጥ የውጭ ሀገር ዜጎች እና ባለቤትነታቸው የውጭ ሀገር ዜጎች የሆኑ የኢትዮጵያ ድርጅቶች በጠቅላላው ከተመዘገቡ የባንኩ አክሲዮን ውስጥ መያዝ የሚችሉት 49 በመቶ ብቻ እንዲሆን ደንግጓል።

በአሁኑ ጊዜ በሸበሌ ባንክ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የያዘው የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ነው፡፡ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ የክልሉ መንግሥት ድርሻውን ቀስ በቀስ ለመቀነስ መወሰኑን ቢገልጹም እስካሁን የተቆረጠ የድርሻ መጠን አልተቀመጠም ብለዋል። በባንኩ ኃላፊዎች መረጃ መሠረት፤ የሸበሌ ባንክ የአክሲዮን ሽያጭ 878 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም የዓመታዊ ዕቅዱን 88 በመቶ ያህል ነው።

የሸበሌ ባንክ ጠቅላላ ሐብት በአሁኑ ጊዜ ከ3 ነጥብ 76 ቢሊዮን ብር ወደ 6 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል፡፡ የተቀማጭ ገንዘብ መጠንም በ70 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ 2 ነጥብ 28 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ባንኩ ከሶማሌ ክልል ባለፈ በድሬዳዋ፣ በሐረር እና በኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፎቹን ከፍቷል። ፎርቹን እንደዘገበው፤ ከከተማ አስተዳደሩ መሬት ለማግኘት ባደረገው ጥረት ባለመሳካቱ፣ ወሎ ሰፈር አካባቢ ባለ ዘጠኝ ፎቅ ሕንፃ በመግዛት ዋና መሥሪያ ቤቱን ወደ አዲስ አበባ አዛውሯል።

ለዚህ መስፋፋት የዲጂታል አማራጮች እንደ ዋነኛ መሣሪያ ሆነው አገልግለዋል። የባንኩ ደንበኞች ቁጥር 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ በ65 ቅርንጫፎች አማካኝነት በዓመት የ41 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር ተከናውኗል። የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ደግሞ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ማዕከላዊው ብሔራዊ ባንክ ባንኮች በተያዘው ዓመት ዝቅተኛ የካፒታል መጠናቸውን 5 ቢሊዮን ብር እንዲያደርሱ የጊዜ ገደብ ማስቀመጡ ያታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ ከሸበሌ ባንክ በተጨማሪ ሦስት ባንኮች ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ባንኮች ዘምዘም፣ ሂጅራ እና ራሚስ መሆናቸው ያታወቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular