የተያዘው የፈረንጆቹ ሜይ ወር በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ መንደሮቻቸው የመመለስ ሕጋዊና ሰብአዊ መብት እንዳላቸው ለዓለም የሚያስታውሱበት ነው፡፡ በዚህ ወር ፍልስጤማውያን እ.አ.አ በ1948 የፈረሱ ከ400 በላይ መንደሮችንና የተፈናቀሉ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ታሪክ ለትውልድ ያስተላልፋሉ፡፡ መታሰቢያው ብዙውን ጊዜ የሚካሄደው በየዓመቱ ሜይ 15 ሲሆን፣ ይህ ቀን ፍልስጤማውያን “የነክባ ቀን” (የታላቁ መቅሰፍት ቀን) ብለው የሚጠሩትና በርካታ የፍልስጤም ግዛትችን በወረራ የያዘችው እስራኤል “የነጻነት” ቀኗን የምታከብርበት ነው።
ለወትሮው ቢሆን ይህ ዓመታዊው የፍልስጤማውያን የ“መመለስ ጉዞ”፤ በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ በእስራኤል ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያንን ያሳትፍ ነበር፡፡ በመርሐ ግብሮቹ በፈረሱ መንደሮቻቸው ውስጥ በተዘጋጁ ጉብኝቶች ላይ ፍልስጤማውያኑ ታሪካቸውን ይዘክራሉ፡፡ በእነዚህ ዝግጅቶች አማካኝነት እስራኤል ማንነታቸውን ለማጥፋት እያደረገች ያለችውን ሙከራ በመቃወም ማንነታቸውን በድጋሚ ስለማረጋገጥም ይታገላሉ፡፡ ይሁንና መርሐ ግብሩ በዚህ ዓመት ሰው አልባ በሆኑ የፍልስጤም መንደሮች ውስጥ ወደሚከናወኑ ትናንሽ የጉዞ መርሐ ግብሮች ተቀይሯል። ለዚህ ዋንኛው ሰበብ የሆነው በእስራኤል ፖሊስ የተጣሉ ገደቦች ናቸው፡፡
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብት ጥበቃ ማኅበር ኀላፊዎች እንደገለጹት፣ የዘንድሮውን መርሐ ግብር እንደ ወትሮው ለማከናወን ከእስራኤል ባለሥልጣናት ጋር የሚደረገው ውይይት የተጀመረው ከጉዞው ሦስት ወራት በፊት ነበር። ነገር ግን ፖሊስ መጀመርያ ላይ ከዝግጅቱ አስተባባሪዎች ጋር ለመነጋገር ፍቃደኛ እንዳልነበረና ሰልፉ የሚቀጥል ከሆነም በኃይል ሊበትነው እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ሰንብቷል፡፡ አስተባባሪዎቹ ለዚህም ምላሽ ይሆን ዘንድ ማኅበሩ “አዳላህ” ከተሰኘው የመብት ተሟጋች ቡድን ጋር በመሆን ለእስራኤል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ በማቅረባቸው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ለጥያቄዎቻቸው ይፋዊ ምላሽ እንዲሰጥ አስገድዶታል።
ውይይቱ ከተጀመረ በኋላም ቢሆን ፖሊስ ነገሮችን የማዘግየትና ቅድመ ሁኔታዎችን የመቀያየር አዝማሚያ ያሳይ ነበር፡፡ ፖሊስ ሰልፉ እንዲካሄድ ፍቃድ ከሰጠ በኋላ ደግሞ የተሳታፊዎች ቁጥር ከአንድ ሺሕ እንዳይበልጥ የሚል ቅድመ ሁኔታ አስቀመጠ፡፡ አስተባባሪዎች ግን ባለፉት ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይታደሙበት እንደነበር በማስታወስ፤ ገደቡን “ምክንያታዊ ያልሆነ” መሆኑን ተከራክረዋል። በተጨማሪም ፖሊስ ማንኛውም የፍልስጤም ሰንደቅ ዓላማ ወይም ብሔራዊ ምልክቶች እንዳይታዩ አግዷል፡፡ ለዚህ ያስቀመጠው ምክንያት “ሁከትን ሊቀሰቅስ ይችላል” በሚል ነው።
አስተባባሪዎች ሰልፉን በተለመደው መልኩ ካከናወኑ፣ በተለይም የፍልስጤም ምልክቶች ከታዩ ሰልፉ ሊታገድና ሊበተን እንደሚችል በግልጽ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ሰልፉ በተለምዶ ቤተሰቦችን፣ ሕፃናትንና አረጋውያንን የሚያሳትፍ በመሆኑ አስተባባሪዎቹ ማስጠንቀቂያውን በቁም ነገር መውሰድ ነበረባቸው። “ሰዎች ከልጆቻቸው ጋር የሚመጡበት ቦታ ነው” ያሉት አስተባባሪዎች፣ የፖሊስ ጣልቃ ገብነት ቢኖር በተሳታፊዎች ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ ጣላቸው፡፡ “ቦታው ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል እንፈልጋለን” በማለት ፖሊስ በሚፈልገው መልኩ አስቀጥለውታል፡፡
ፍቃዱ የተሰጠው ጉዞው ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት በመሆኑም በተለያዩ ቦታዎች ወደሚከናወኑ ትናንሽና የተበታተኑ መርሐ ግብሮች ተቀይሮ ቀድሞ የፍልስጤም ማኅበረሰቦች ይኖሩባቸው በነበሩትና በኃይል እንዲለቁ በተደረጉ እንደ አል ዳሙን፣ ሚያር፣ ማሉል፣ አል ላጁን እና ሚስካ ባሉ ከ30 በላይ ሰው አልባ መንደሮች ተካሄዷል፡፡ ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ የተሳታፊዎች ቁጥር ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ይለያያል። በአንዳንድ ቦታዎች ዐስር ሰዎች ሲገኙ፣ በሌሎች ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገኝተዋል። በአል ዳሙን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዋናው ዝግጅት ላይ የተሳተፉ ሲሆን፣ በሌሎች ቦታዎች ግን በተፈጠረው የአደረጃጀት ችግርና በዝግጅቶቹ መበታተን ምክንያት የተሳታፊዎች ቁጥር ውስን ነበር። በሚስካ በተካሄደው አነስተኛ ስብሰባ ላይ የነበሩት 70 ተሳታፊዎች መካከል የጥንቶቹ ነዋሪዎች ቤተሰቦችና ዝርያዎችም ይገኙበታል። ከእነዚህም መካከል ለዜና ምንጩ የተናገሩት ዕድሜያቸው በ80ዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኘው አንድ አዛውንት፤ በልጅነታቸው ከመንደሩ ስንፈናቀል “ተመልሰን የምንመጣ መስሎን ነበር የሄድነው” ብለዋል፡፡ ሆኖም እስካሁንም ሳይመለሱ ኑሯቸው የስደት ሆኗል፡፡ የአዛውንቱ መንደር የፈረሰው በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ ይህ ጊዜ በመንደሩ ያሳለፉት የልጅነት ጊዜያቸው ማብቂያ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ጥቂቶችን ብቻ ባሳተፈው በዘንድሮው የመመለስ ጉዞ የተሳታፉት የነክባ ተፈናቃዮች ብቻ ሳይሆኑ ሦስተኛ ትውልዶች ጭምር ናቸው፡፡ ከተሳታፊዎች መካከል የሆነችው ያስሚን ሽቢታ የተባለች ወጣት፣ ወደ ፈረሱት መንደሮች መመለስ በትዝታ ብቻ ሳይሆን በምናብም የታገዘ መሆኑን ገልጻለች። “መንደሩ ባይፈርስ ኖሮ ምን ሊሆን ይችል እንደነበር በምናቤ እያየሁ እንደ ሕያው ቦታ ለመሳል እሞክራለሁ” ብላለች። መኖሪያ ቤቱ መልሶ ባይገነባም እንኳ፤ ታሪኩን ለልጆች ማስተላለፍ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጻለች። “[በምናባችን] ፍጹም ጥፋት የሚባል ነገር የለም፤ ሁልጊዜም ፍርስራሾች ይኖራሉ፣ ሰዎችም ወደ ፍርስራሾቹ በመመለስ አዲስ ትርጉም ለመሥራት ይሞክራሉ” ብላለች።
የዘንድሮው ጉዞ መልክ ቢቀይርም አስተባባሪዎችና ተሳታፊዎች መልእክቱ እንዳልተቀየረ ይናገራሉ፤ ይህም ከመሬታቸው ጋር ያላቸው ቁርኝትና የመመለስ ጥያቄያቸው ምንም ዓይነት እንቅፋት ቢገጥመውም እንደማይቋረጥ በማስረገጥ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












