Homeዜናና ወቅታዊዜናየስፔን ኮንግረስ ከሞሮኮ ጋር በምትካለለው በሴውታ ግዛት የሚኖሩ ሙስሊሞች የቀድሞ ሥማቸውን መጠሪያ...

የስፔን ኮንግረስ ከሞሮኮ ጋር በምትካለለው በሴውታ ግዛት የሚኖሩ ሙስሊሞች የቀድሞ ሥማቸውን መጠሪያ እንዲመልሱ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ አጸደቀ

የስፔን ኮንግረስ የፍትሕ ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባ፤ በሴውታ ከተማ የሚኖሩ ሙስሊሞች የቀድሞ ሥማቸውን መጠሪያ ወደነበረበት እንዲመልሱ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በመደገፍ አጽድቋል፡፡ ከተማዋ በስሜን አፍሪካ የባህር ዳርቻ ላይ የምትገኝ የስፔን ግዛት ስትሆን፣ ከዋናው የስፔን ምድር በጂብራልታር ወሽመጥ ተለይታ ትገኛለች።

ኮንግረሱ በግራ ዘመሙ ፖዴሞስ ፓርቲ በኩል የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በ19 ድጋፍ፣ በ3 ተቃውሞ እና በ15 ድምጸ ተአቅቦ አጽድቋል። ድምጽ የተሰጠበት የውሳኔ ሐሳብ እ.አ.አ በ1980ዎቹ የሴውታ ሙስሊም ነዋሪዎች የስፔን ዜግነት በሚያገኙበት ወቅት የቀድሞ “የዐረብ እና ሙስሊም” መጠሪያ ሥማቸውን እንዲለውጡ የሚያስገድደውን አሠራር የሚሽር ነው፡፡

የጸደቀው የውሳኔ ሐሳብ የሲቪል መዝገብ ደንቦች እንዲሻሻሉ እና ቤተሰቦች በነጻና በቀላል ሂደት የቀድሞ ሥማቸውን እንዲመልሱ የሚፈቅድ ልዩ አሠራር እንዲዘረጋ ይጠይቃል። በኮንግረሱ ከቀኝ አክራሪው ቮክስ ፓርቲ በስተቀር ሁሉም የፓርላማ ቡድኖች የውሳኔ ሐሳቡን ደግፈውታል፡፡ የሴውታ አካባቢ ምክር ቤትም ከዐስር ዓመት በፊት ይህንኑ ሐሳብ በሙሉ ድምጽ ደግፎት እንደነበር ሞሮኮ ወርልድ ኒውስ ዘግቧል።

በውሳኔው ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የ”ሴውታ ያ” ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ሙሐመድ ሙስጠፋ፤ “በሺሕዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ማንነታቸው ተቆርጦ ቀርቷል” ሲሉ ውሣኔው ለበርካታ ዐስርት ዓመታት የደረሰባቸውን መድልዎ የሚቀለብስ “ታሪካዊ ፍትሕ [የሰፈነበት]” መሆኑን ገልጸዋል። የውሳኔ ሐሳቡ የስፔን መንግሥት “አስተዳደራዊ ስሕተቱን በይፋ እንዲቀበል ያደርጋል” ያሉት ሙስጠፋ፤ “የማኅበረሰቡን ክብር ለመመለስ ተቋማዊ ይቅርታ መጠየቅ” አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የውሳኔ ሐሳቡ በኮንግረሱ ቢጸድቅም ተግባራዊ ለማድረግ አሁንም የመጨረሻው የመንግሥት ውሳኔ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። በሴውታ የሚኖሩ ሙስሊሞች የከተማዋን የሕዝብ ቁጥር ከ40 በመቶ በላይ ይሸፍናሉ፡፡ በአብዛኛው የሞሮኮ እና የስፔን የዘር ግንድ ያላቸው የማኅበረሰብ አባላት ናቸው። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular