Homeዜናና ወቅታዊዜናበመካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋት ሳቢያ የሐጅ ተመን ላይ ጭማሪ እንደማይደረግ የጠቅላይ ምክር ቤቱ...

በመካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋት ሳቢያ የሐጅ ተመን ላይ ጭማሪ እንደማይደረግ የጠቅላይ ምክር ቤቱ የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ተናገሩ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ የ1447 ዓ.ሂ የሐጅ ጉዞ የመጀመሪያ በረራ ግንቦት 2/2018 እንደሚሆን አስታውቋል፡፡ ይህንኑ የምክር ቤቱ የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ሐጅ ዓብዱልፈታህ ሙሐመድ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው በአሁኑ ሰዐት በተፈጠረው በመካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋት ሳቢያ የሐጅ ተመን ላይ ጭማሪ እንደማይኖርም ገልጸዋል፡፡ “በዋጋ ተመኑ ላይ ሑጃጁ ተመዝግበው ሳዑዲ ደርሶ እስኪመለሱ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሊኖር የሚችለው የገበያ ሁኔታና ሊከሰት የሚችል የምንዛሬ ልዩነት ከግምት ገብቷል” ብለዋል፡፡ “ከዚህ አኳያ ሑጃጁ ደርሰው እስኪመለሱ ድረስ ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ አይኖርም ብለን እንጠብቃለን” ሲሉ ለ“ሚንበር ቲቪ” አስረድተዋል፡፡

በዘንድሮ ሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ከመላው ዓለም ወደ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ሑጃጅ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከኢትዮጵያም ከአምስት ሺሕ በላይ ምዕመናን ተመዝግበዋል፡፡ ከሀገሮች መካከል ኢንዶኔዥያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ቢጨምርም፣ በዘንድሮ ሐጅ የጉዞ ዋጋ ላይ ለአንድ ተጓዠ 117 የአሜሪካ ዶላር ቅናሽ እንደምታደርግ ከቀናት በፊት አስታውቃለች፡፡

የሳዑዲ ዐረቢያ  ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር  ይፋ ባደረገው  የምዝገባ  የጊዜ ሠሌዳ    መሠረት፤ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከኅዳር 22 እስከ ጥር 18/2018 ድረስ በሠላሳ  የሐጅ ጉዞ ማዕከላት   ምዝገባ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ በመጋቢት ወር መጨረሻ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ሙሐመድ ሷሊህና ልዑካቸው አገልግሎት ለመስጠት ውል ከፈረመው ድርጅት ጋር ውይይት አካሄደዋል፡፡

ውሉን ከፈረመው “መሻሪቅ አልማሲያ” የመዲናው ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮች ጋር በተደረገው ውይይት በመዲና እንግዶችን በክብር ተቀብሎ ከማስተናገድ እንዲሁም ቆይታቸውን የሰመረ በማድረግ በአግባቡ ከመሸኘት አንጻር እየተደረገ ስላለው የቅድመ ዝግጅት ግምገማ ተደርጓል፡፡

ኃላፊው ከ“ሚንበር ቲቪ” ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፤ ለሁሉም ሑጃጅ ቪዛ እና ትኬት መሠራጨቱን በመጥቀስ፤ ሑጃጅ በተመደቡላቸው አሚሮች በኩል ሥልጠና እንደሚወስዱ ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በሳዑዲ አየር መንገድ በሚደረጉት ተከታታይ የስምንት ቀናት በረራዎች የመጀመሪያዎቹ 270 ሁጃጆች ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከ1 ወር እስከ 45 ቀናት ይወስድ የነበረው የመመለሻውን ቀን በመቀነስ በአንድ ሣምንት ውስጥ ምዕመናን እንደሚመለሱ አስረድተዋል፡፡

የዘንድሮ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ከግንቦት 17 እስከ ግንቦት 22/2018 ባለው ጊዜ ውስጥ ይከናወናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የዓረፋ ቀን ደግሞ ግንቦት 18 ቀን ይውላል ተብሎ ይጠበቃል። የሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት ቦታ ላማስያዝ እና የቪዛ ሂደቶች “ኑሱክ ሐጅ” በተሰኘው መተግበሪያ ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular