Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችየአክሱም ሙስሊሞች ጉዳይ ዓለማዊ (Secular) መንግሥት እንዲሰፍንና የዜጎች እኩልነት በቃል ብቻ ሳይሆን...

የአክሱም ሙስሊሞች ጉዳይ ዓለማዊ (Secular) መንግሥት እንዲሰፍንና የዜጎች እኩልነት በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር እንዲረጋገጥ ከሚሹ ኃይሎች ሁሉ ጋር ተባብሮ መሥራትን የሚጠይቅ ነው” – የታሪክ አጥኚው አሕመዲን ጀበል

በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ባለፈው ሣምንት ለጁመዐ በተሰባሰቡ ምዕመናን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን፤ መስጂዶች በኃይል ተሰብረው የተከበረው ቅዱስ ቁርኣን ተቀዷል፡፡ ጉዳዩን በማስመልከት መግለጫ ያወጣው የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ ጥቃቱ አስቀድሞ “በማኅበራዊ ሚዲያዎችና በተለያዩ መድረኮች ሲሰራጩ የቆዩ የጥላቻ ስብከቶች ውጤት” መሆኑን አስታውቋል። በእነዚህ ስብከቶች “ሒጃብ ይከልከል” ከሚለው ባለፈ፣ “ለዘመናት የቆየውን የአዛን የድምፅ ማጉያ አጠቃቀም” በኃይል ለማስቆም የተደረገው ወታደራዊ ጥሪ ሕገ መንግሥታዊ የእምነት ነፃነት መብትን የሚጥስ ነው ብሎታል።

በዕለቱ በከተማዋ የፀጥታ አካላት የተወሰደው የድምፅ ማጉያዎችን የመንጠቅ ርምጃን ተከትሎም በተደራጁ አካላት ለሰላት በወጡ ምዕመናን ላይ የተፈጸመው የድንጋይ ውርወራና ድብደባ ምንም ዓይነት ሕጋዊ አመክንዮ የሚቀርብለት አለመሆኑንም ገልጿል። በሰላማዊ አማኞች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን የገለጸው ከፍተኛ ምክር ቤቱ፤ የመስጅድ አባላት ሕገ ወጥ እስርን በጥብቅ በመኮነን “መንግሥት በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገባ” ጥሪ አቅርቧል።

በወቅቱ ጥቃቱ የተመራው በፀጥታ ኃላፊው ቴዎድሮስ በየነ አማካኝነት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡ ምክር ቤቱ በዚህ መግለጫው፤ በተፈጸመው ጥቃት “እጃቸው ያለበት የፀጥታ አካላትና ሲቪሎች በአስቸኳይ ተይዘው ለሕግ እንዲቀርቡ” ጠይቋል።

በከተማዋ በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት ለብሔራዊ ፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች በሒጃብ ምክንያት ከተምህርት ገበታ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ይህን ተከትሎም በመቀለ ከተማ ድርጊቱን በመቃወም ሰላማዊ ሠልፍ መደረጉ ይታወሳል፡፡

በተደጋጋሚ ሙስሊሞች ላይ እንግልት የሚፈጸምበትን የአክሱም ከተማን ጉዳይ በማስመልከት ዘለግ ያለ ጽሑፍ ያጋሩት በኢትዮጵያ ሙስሊሞች የታሪክ ጥናት መጽሐፍት የሚታወቁት አሕመዲን ጀበል፤ ጉዳዩ ለበርካታ ዓመታት የቆየ መሆኑን በመጥቀስ፤ “[ነገሩ] ቀለል ያለ የሃይማኖት ግጭት ሳይሆን” በአንድ እምነት የበላይነት ላይ የተገነባና ሙስሊሙን እንደ “ባዕድ” የሚቆጥር “የአፓርታይድ መዋቅር ውጤት ነው” ብለዋል፡፡

የዚህ ሥርዓት ባለቤቶችና ደጋፊዎቻቸው ሙስሊሙ እኩል ዜግነትንና የሴኩላር ሕገ መንግሥት መከበርን ሲጠይቅ፣ በአክሱም “ሕገ መንግስቱን ጭምር የተቃረነው አፓርታይዳዊ አገዛዝ” እንዲቀጥል የሚፈልጉ አካላት ምላሻቸው ቀጥተኛ አለመሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ከዚያ ይልቅ “የሴራ ትርክት በመምዘዝ” የዓለማዊ ሕገ መንግሥትና የሕግ የበላይነት እውን ሆኖ መብታቸው እንዲከበር የሚጠይቁ አካላት ላይ “የሐሰት ፍረጃ” እንደሚነዛባቸው አብራርተዋል፡፡

አክለውም በአክሱም ምድር የሀገሪቱ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትም ሆነ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች “በተግባር ዋጋ አጥተው ተጥለዋል” ያሉት አጥኚው፤ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ እየታየ ያለው ሁኔታ ሕግን መሠረት ያደረገ ሳይሆን፣ አንዱን እምነት “ባለቤት” ሌላውን ደግሞ “ባዕድ” የሚያደርግና በመዋቅር የተደገፈ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ረገድ እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት “ላዩን ለሚታዩ ምልክቶች ምላሽ ከመስጠት ወጥቶ፣ ችግሩ ሥር እንዲሰድ የሚያደርጉትን መዋቅራዊ መሠረቶችና የሰፈነውን አግላይ አስተሳሰብ የሚቀይሩ ሥልታዊ የትግል መንገዶችን መቀየስ የግድ መሆኑን” አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡  

ይህ ትግል የአንድ ሰሞን ጩኸት ወይም የአክሱም ሙስሊሞች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ በመላ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ሃይማኖታዊ ጫና ነጻ የሆነ ዓለማዊ (Secular) መንግሥት እንዲሰፍንና የዜጎች እኩልነት በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር እንዲረጋገጥ ከሚሹ ኃይሎች ሁሉ ጋር ተባብሮ መሥራትን እንደሚጠይቅም አስገንዝበዋል፡፡

በአክሱም ከተማ ባለፈው ሣምንት ጁመዐ ሚያዝያ 2/2018 በምእመናን ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የከተማው የጸጥታም ሆነ የአስተዳደር መዋቅር ያለው ነገር የለም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular