Homeዜናና ወቅታዊዜናየአክሱም ከተማ የፀጥታ ኃላፊ በመሩት ርምጃ ለጁመዐ ሰላት በተሰባሰቡ ምዕመናን ላይ ጥቃት...

የአክሱም ከተማ የፀጥታ ኃላፊ በመሩት ርምጃ ለጁመዐ ሰላት በተሰባሰቡ ምዕመናን ላይ ጥቃት ተፈጸመ

  • “እንደአባዋ” በመባል የሚጠራ ሥፍራ የሚገኘውን መስጂድ ተሰብሮ ቅዱስ ቁርኣን ተቀዷል

በትግራይ ክልል አክሱም፤ በዛሬው እለት ለጁመዐ ሰላት በተሰባሰቡ ምዕመናን ላይ የከተማዋ የፀጥታ ኃላፊ ቴዎድሮስ በየነ በመሩት ርምጃ በርካቶች ላይ ጥቃት ተሰንዝሮ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ምዕመናን ውስጥ ሁለቱ ላይ የደረሰው የአካል ጉዳት ከባድ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በነዋሪዎች መረጃ መሠረት፤ ከጁመዐ ሰላት በፊት የአካባቢው ምዕመናን ለሰላት ዝግጅት እያደረጉ በነበረበት ወቅት፤ የፀጥታ ኃላፊው የመሩት ቡድን ለሰላት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ሸራ እና የድምጽ ማጉያዎችን ነጥቀው ወስደዋል፡፡ ይህን በፀጥታ ኃላፊውን ድርጊት ተከትሎ ከሰላት በኋላ ምዕመናን ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ በዚህ ወቅት በምዕመናን ላይ የተለያየ ጥቃት ተሰንዝሯል፡፡

እነዚሁ ነዋሪዎች ከሰላቱ መጠናቀቅ በኋላ “የፀጥታ አካላት እና የከተማው ወጣቶች” ምዕመናን ተከራይተው የሚሰግድዱበትን “እንደአባዋ” በመባል የሚጠራ ሥፍራ የሚገኘውን መስጂድ ሰብረው በመግባት ቅዱስ ቁርኣን መቅደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በመስጂዱ ውስጥ የነበሩ የመስጂድ ኢማሞችን እና ምዕመናንን በበትር እና በድንጋይ ድብደባ ፈጽመውባቸዋል፡፡ ከዚህ ድርጊት በኋላ በከተማዋ ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ በርካታ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል።

በምዕመናን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መቀመጫውን መቀለ ከተማ ያደረገው የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ኃላፊዎች ድርጊቱን ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ዘጠኝ ሰዐት ገደማ ከአጎራባች ከተሞች ተጨማሪ የፀጥታ ኃይል ገብቷል ተብሏል፡፡ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ምዕመናን በከተማው በሚገኘው ቅድስት ማርያም ሆስፒታል የሕክምና ድጋፍ ማግኘታቸው ተሰምቷል፡፡ ከተጎጂዎቹ መካከል ስድስቱ ወዲያውኑ የሕክምና ድጋፍ አግኝተው ሲመለሱ የሁለቱ ጉዳት ከባድ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ጥቃቱን በተመለከተ የትግራይ ክልል የፀጥታ አካላት እስካሁን ድረስ ያሉት ነገር የለም፡፡

በአክሱም ከተማ ባለፈው ዓምት ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በትምሕርት ቤቶች በተጣለው ሒጃብ ክልከላ ምክንያት ከትምሕርት ገበታ ውጪ መሆናቸው ያታወሳል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular