Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችየኢራን እና አሜሪካ ባለሥልጣናት ወደ “ሰላም ማደሪያዋ” መዲና ተጉዘዋል

የኢራን እና አሜሪካ ባለሥልጣናት ወደ “ሰላም ማደሪያዋ” መዲና ተጉዘዋል

ዋሽንግተን “ታላቁ ቁጣ” (Epic Fury) ስትል የጠራችው፤ ቴህራን ደግሞ “እውነተኛው ቃል ኪዳን” (True Promise) በሚል የሠየመችው ጦርነት፤ በአርባኛ ቀኑ በፓኪስታን አሸማጋይነት በቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት ጋብ ብሎ ሁለት ቀናት ተቆጠሩ። ለሁለት ሣምንታት በሚቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት፤ ተደራዳሪዎቹ “ምንም ዓይነት ሚሳኤልም ሆነ የአየር ጥቃት አንፈጽምም” ብለው ተማምለዋል፡፡ ለቀጣይ ድርድር በአካል ይገናኛሉ ተብሎ የሚጠበቀው ነገ ቅዳሜ ሚያዝያ 3/2018 ነው፡፡

የመካከለኛው ምሥራቅን ቀጠና ያወደመውን ጦርነት ልጓም ሊያበጅለት ይችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን ይህን ታሪካዊ ድርድር ለማስተናገድ የተመረጠችው የፓኪስታን መዲና ኢስላምአባድ ነች፡፡ መዲናዋ ለዚህ ዝግጅት የከተማውን አውራ ጉዳናዎች በከፍተኛ የጸጥታ አጀብ ቁጥጥር ስር አውላለች። ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፤ በኢስላምአባድ ትናንት ሐሙስ እና ዛሬ ጁመዐ መንገዶቹ ባልተለመደ ሁኔታ ጭር ብለው ታይተዋል። በአውራ ጎዳናዎች ላይ በብዛት የሚርመሰመሱት የጦር ሠራዊት አባላትና የፈጥኖ ደራሽ ታጣቂዎች ናቸው፡፡

የፓኪስታን ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ ዋና ዋናዎቹ የሁለቱ ሀገሮች ልዑካን ተጠቃለው የሚገቡት በዛሬው እለት ነው፡፡ በአሜሪካ በኩል የድርድር ቡድኑ ልዩ መልዕክተኞቹ ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነርን በማካተት በምክትል ፕሬዝዳንት ጄ ዲ ቫንስ እንደሚመራ ዋይት ሐውስ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡

የኢራን ባለሥልጣናት ልዑካቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ዓባስ አራቅጂን እና የፓርላማ አፈ ጉባኤውን ሙሐመድ ባገር ጋሊባፍን እንደሚያካትት ገልጸዋል። የኢራን ዓብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አመራሮች በድርድሩ ላይ ይገኛሉ፡፡ የጦርነቱ ዳፋ የተረፋቸው ኳታር እና ሳዑዲ ዐረቢያን ጨምሮ የባሕረ ሰላጤው ሀገሮች ልዑካን ወደ ኢስላምአባድ ተጉዘው፤ በጎንዮሽ ውይይቶች ላይ ሊሳተፉ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

ከፍተኛ የጸጥታ ሥጋት በመኖሩ ምክንያት፣ ወሳኙ ስብሰባ ሊደረግባቸው የሚችሉ ከሦስት እስከ አራት የሚደርሱ አማራጭ ሥፍራዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከፍተኛ ሥልጣን የደረቡ የድርድሩ ተሳታፊዎች በኢስላማባድ በሚገኘውና ለየት ያሉ እንግዶች ብቻ በሚስተናገዱበት ባለ አምስት ኮከቡ ሴሬና ሆቴል ያርፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በርግጥ ድርድሩም እዚያው ሊካሄድ እንደሚችል ይገመታል። ሌሎች ሥፍራዎችም በአማራጭነት ተይዘዋል፡፡ ድርድሩ ምን ያህል ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል የተቀመጠ የጊዜ ሠሌዳ ባይኖርም፤ ረቡዕ ዕለት ከሴሬና ሆቴል እንዲወጡ የተደረጉ እንግዶች፣ ሆቴሉ እስከ እሑድ ምሽት ድረስ እንደተያዘ ተነግሯቸዋል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular