በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከ22 ዓመት በፊት የተመሠረተው የነጃሺ ኢስላሚክ ትረስት፤ በእሳት መውደሙን የትረስቱ ምክትል አሚር ዓሊ ዓብደላ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ የእሳት አደጋ የደረሰበት መጋቢት 29/2018 ነው፡፡
በጆሐንስበርግ ሜይፊይር በመባል በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ማዕከሉ፤ ነዋሪነታቸውን በከተማው ላደረጉ ኢትዮጵያውያን ሠርግ እና ሐዘንን ጨምሮ ለማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሁም ከሦስት መቶ በላይ ታዳጊዎች የቁርኣን ጥናት የሚከታተሉበት መሆኑን ምክትል አሚሩ አስረድተዋል፡፡

በአደጋው በማዕከሉ ውስጥ የነበሩ የቢሮ መገልገያዎችና ቁሳቁስ፣ ሌሎች ንብረቶች እና ሠነዶች ተቃጥለዋል፡፡ ነገር ግን በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩ ተገልጿል፡፡ የትረስቱ ምክትል አሚር ዓሊ ዓብደላ፤ በአደጋው ውድመት የደረሰበትን ማዕከል መልሶ ለመገንባት፤ በጊዜያዊነት ከአባላት መዋጮ እየተሰበሰበ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ ሥፍራውን በማጽዳት የሕንጻ ንድፍና የሌሎችም ጉዳዮች ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ወደ ግንባታ ሲገባ የሚሰበሰብ ገንዘብ ቃል እየተገባ ነው ብለዋል፡፡
ነጃሺ ትረስትን ለማገዝ ከሚፈልጉ በሌሎች ሀገሮች ከሚገኙ ሙስሊም የኢትዮጵያ ኮሚኒቲዎች ጋር የሚኖረው የገቢ ማሰባሰቢያ በቀጣይ እንደሚከናወንም ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡ እ.አ.አ በ2008 የተመሠረተውን ነጃሺ ኢስላሚክ ትረስት የእሳት አደጋ መንስኤ ለማጣራት የሜይፌይር ፖሊስ ምርመራ መጀመሩ ታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) እ.ኤ.አ. በ2024 ባወጣው ግምት እንዳመለከተው፤ 200 ሺሕ ገደማ ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ ይኖራሉ። ከኢትዮጵያ ወደ ሀገሪቱ የሚወስደውን “የደቡብ መስመር” ያጠኑ ተመራማሪዎች እንዳሉት ደግሞ በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ ያመራሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ መፍለስ የጀመሩት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ በ1994 የአፓርታይድ ሥርዓት ሲያበቃ ፕሬዝዳንት ሆነው ሀገሪቱን ለሌሎች አፍሪካውያን ክፍት ካደረጉ ወዲህ መሆኑ ይነገራል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












