የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ዳይሬክተሮች ዳይሬክተር አቶ በላይ ቱሉ፤ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ እና ለመስኮት የኢንሹራንስ አገልግሎት ሰጪዎችን የሕግ ማዕቀፍ ለማሻሻል የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ይህን ያሉት “በኢትዮጵያ የተካፉል ሥነ ምህዳርን መዘርጋት” በሚል ርእስ ‘ሴንተር ፎር አንክሉሲቭ ኤንድ ሰስተኔብል ፋይናንስ’ ከኤፍ ኤስ ዲ ኢትዮጵያ ጋር ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡
በአዲስ አበባ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከተሳታፊዎች “ተካፉል” በጅማሮ ላይ ያለ በመሆኑ፤ ሕጉን ለማሻሻል አስቻይ የሆነ የሕግ ማዕቅፍ እንዲኖር ምን ለማድረግ ታስቧል የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ “ገና ለውይይት አልቀረበም” ባሉት አዋጅ ላይ ራሱን በቻለ ክፍል መካተቱን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ማዕከላዊ ባንኩ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ብሔራዊ የወለድ አልባ ፋይናንስ ስትራቴጂ እያዘጋጀ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል። በስትራቴጂው ከታቀፉት ውስጥ የፋይናንስ አገልግሎት “ተካፉል” በመባል የሚጠራው ከወለድ ነጻ የኢንሹራንስ አገልግሎት አንደኛው መሆኑን ገለጸዋል፡፡ ስትራቴጂው የሕግና ቁጥጥር ማዕቀፎችን፣ የታክስ ጉዳዮችን፣ የሸሪዓ አሰተዳደርና ተዛማጅ ጉዳዮችን ያካተተ እንደሚሆን አብራርተዋል። በተጨማሪም የሰው ኃይል ልማትን እና የወለድ አልባ መሠረተ ልማትን ያካተተ ነው ብለዋል።

በመድረኩ ላይ በኢትዮጵያ በአሁኑ ስዐት በመስኮት ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡ ስምንት ከወለድ ነጻ አገልግሎት ሰጪ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቢኖሩም እስካሁን ሙሉ በሙሉ ሸሪዓን መሠረት ያደረገ የኢንሹራንስ አገልግሎት ሰጪ በገበያው ላይ አለመኖሩን ክፍተት መፍጠሩ ተገልጿል፡፡ በእንቅስቃሴ ላይ ከሚገኙት መካከል “አማና” ኢንሹራንስ በሒደት ያለ እና እስካሁን አገልግሎት አለመጀመሩ ተጠቁሟል።
መድረኩን ያዘጋጀው የሴንተር ፎር አንክሉሲቭ ኤንድ ሰስተኔብል ፋይናንስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢብራሂም ዓብዱልዓዚዝ ለ“ሚንበር ቲቪ” እንደተናገሩት፤ የዛሬው መድረክ ድርጅቱ ከወለድ ነጻ የፋይናንስ የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያዎች ላይ የሚሠራቸው ሥራዎች አካል ነው፡፡ በዚህ ሒደት በተለይ ዘርፉ እንዳያድግ የፖሊሲ ማነቆዎች ዋንኛ ተግዳሮት መሆኑን በመጥቀስ ይህ እንዲሻሻል እንደሚሠሩም ጠቁመዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የብሔራዊ ባንክ ተወካዮች፣ የእስላማዊ ኢንሹራንስ ኃላፊዎች፣ ፖሊስ አውጪዎችና ምሑራን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












