Homeዜናና ወቅታዊዜናከሰላም ስምምነቱ ጀርባ - የሙጅተባ ኹመይኒ የመጨረሻው ማሕተም እና የዊትኮፍ “ንዴት”

ከሰላም ስምምነቱ ጀርባ – የሙጅተባ ኹመይኒ የመጨረሻው ማሕተም እና የዊትኮፍ “ንዴት”

አሜሪካ እና እስራኤል በጣምራ ኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት፤ በ40ኛው ቀን ለሁለት ሣምንት በተደረሰ የተኩስ አቁም ስምምነት ጋብ ብሏል፡፡ ፓኪስታን ዋና አሸማጋይ ሆና በመራችው ድርድር፤ ግብጽ እና ቱርክ ተደራዳሪዎችን የመግባባት ሚና ተወጥተዋል፡፡ ለተኩስ አቁም ስምምነቱ አሜሪካ አስቀድማ ባለ ዐስራ አምስት ነጥብ ምክረ ሐሳብ ብታቀርብም፤ በመጨረሻ ኢራን ሌላ ባለ ዐሥር ነጥብ ምክረ ሐሳብ የአደራዳሪዎች ጠረጴዛ ላይ አስቀምጣለች፡፡ የዚህ ስምምነት ዋና አስኳል፤ ኢራን የሁርሙዝ መተላለፊያን ስትከፍት፤ በምላሹ የአሜሪካን ጥቃት ማስቆም ነው፡፡

በሁርሙዝ ወሽመጥ ላይ የየብስ ግዛት መብትን (Territorial rights) በጋራ የያዙት ኢራን እና ኦማን፤ እስከ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚደረስ የትራንዚት ክፍያ እንዲያስከፍሉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ኢራን ይህን ገንዘብ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ትጠቀምበታለች፡፡ በዚህ ምክረ ሐሳብ ውስጥ የተካተቱት ሌሎች ነጥቦች የጦርነት ኪሳራ ካሣ፣ እርስ በርስ ላለመጠቃቃት የሚገቡ ግዴታዎች እና ማንኛውም ስምምነት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የውሳኔ ሐሳብ አማካኝነት እንዲጸድቅ የሚሉትን ያካትታል። በኢራን ላይ የተጣሉ ሁሉም ማዕቀቦች እንዲነሱ የሚጠይቀውም በሠነዱ ላይ ሠፍሯል፡፡

በድርድሩ ላይ የፓኪስታን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አሲም ሙኒር፣ ለጉብኝት ሀንጋሪ የሚገኙት የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ፣ ልዩ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ እና የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዓባስ አራቅጂ ዋንኞቹ ተዋንያን ነበሩ፡፡

በድርድሩ ሒደት ለትራምፕ ቅርብ የሆኑ ምንጮች የተኩስ አቁም ስምምነቱ እስኪታወጅ ድረስ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ርግጠኛ አልነበሩም ተብሏል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ቀነ ገደብ በማስቀመጥ ዛቻውን በመቀጠላቸው፤ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ኃይሎች እና የፔንታጎን ባለሥልጣናት በመጨረሻዎቹ ሰዓታት በኢራን መሠረተ ልማቶች ላይ መጠነ ሰፊ የቦምብ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጁ፤ ትራምፕ ወዴት ሊያዘነብሉ እንደሚችሉ ለማወቅም ሙከራ ሲያደርጉ ነበር።

ኢራን ያቀረበችው ባለ አስር ነጥብ ምክረ ሐሳብ የደረሰው በዚህ መሃል ነው፡፡ በስልክ ተደጋጋሚ ንግግሮችን ሲያደርጉ የነበሩት የትራምፕ ልዩ መልእክተኛ ስትቭ ዊትኮፍ፤ የኢራን ምክረ ሐሳብ “አደገኛ” መሆኑን ለአሸማጋዮች ነግረዋቸዋል፡፡ ሰኞ እለት የፓኪስታን አሸማጋዮች በዊትኮፍ እና በኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዓባስ አራቅጂ መካከል የሚሻሻሉ አዳዲስ ረቂቆችን ሲያመላልሱ፣ የግብፅ እና የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደግሞ ልዩነቶችን ለማጥበብ ጥረት ሲያደርጉ ውለዋል፡፡ አሸማጋዮቹ ለሁለት ሣምንታት ለሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት የቀረበውን የተሻሻለ የውሳኔ ሐሳብ ለአሜሪካ አቅርበው ይሁንታ ማግኘት የቻሉት ሰኞ ምሽት ላይ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የመጨረሻው ውሳኔ በጦርነቱ አባታቸውን ያጡት አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሙጅተባ ኹመይኒ እጅ ላይ ወድቋል፡፡

የጠቅላይ መሪው ተሳትፎ ምሥጢራዊና አድካሚ እንደነበር ተነግሯል፡፡ ከእስራኤል ሊሰነዘርባቸው የሚችለውን የግድያ ሙከራ በመፍራት፣ ኹመይኒ በዋናነት መልዕክት የሚያስተላልፉት በመሃል ባሉ ሰዎች አማካኝነት አጫጭር ማስታወሻዎችን እየላኩ ነበር፡፡ በዚህ መሃል ቻይና ኢራን ከግጭቱ የምትወጣበትን መንገድ እንድትቀይስ ምክር ስትለግሥ ነበር፡፡ በሒደቱ አራቅጂ ድርድሩን በመምራትም ሆነ የአብዮታዊ ጥበቃ አዛዦች ስምምነቱን እንዲቀበሉ በማሳመን ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። ነገሩ ውሎ ሲያድር ሰኞ እና ማክሰኞ የተላለፉ ዋና ዋና ውሳኔዎች ሁሉ የማሳረጊያውን ማሕተም ያሳረፉት ኹመይኒ ናቸው፡፡

በአሜሪካ በኩል ምክትል ፕሬዝዳንት ቫንስ ሀንጋሪ ሆነው በስልክ የሚነጋገሩት ከፓኪስታን ዲፕሎማቶች ጋር ነበር፡፡ በጦርነቱ ከአሜሪካ ጀርባ ግፊት የምታደርገው እስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ቀኑን ሙሉ ከትራምፕና ቡድናቸው ጋር ተደጋጋሚ ንግግር ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም፤ ሒደቱ ከቁጥጥራቸው እየወጣ በመሆኑ ሥጋታቸው እያየለ መጥቶ ነበር፡፡ 

ኢራን እና አሜሪካ ለሁለት ሣምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እየተቀራረቡ መሆኑን ይበልጥ ተስፋ ሰጪ መሆኑ የታየው ማክሰኞ እኩለ ቀን አካባቢ ነው፡፡ ከሰዓታት በኋላ ደግሞ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሸሪፍ የስምምነቱን ዝርዝር በኤክስ ገጽ ላይ ይፋ በማድረግ ሁለቱም ወገኖች እንዲቀበሉት ጥሪ አቀረቡ። በዚህን ጊዜ የትራምፕ ጽንፈኛ አጋሮች ስምምነቱን ውድቅ እንዲያደርጉ የሚያሳስቡ የጽሑፍ መልዕክቶችን ወዲያውኑ ማጉረፍ ጀምረዋል፡፡ ትራምፕ ምን ሊወስኑ ይችላሉ የሚለው በዙርያቸው ባሉ ሰዎች ጭምር ውሳኔ እስኪተላለፍ ድረስ ባሉት ከአንድ እና ሁለት ሰዐት በፊት ጭምር ግራ አጋቢ ነበር ተብሏል፡፡ በቅርብ ያሉ ሰዎች በዚህ መነሻ ስምምነቱ ውድቅ ያደርጋሉ የሚል እምነት የነበራቸው ቢሆንም ፕሬዝዳንቱ ስምምነቱን ተቀብለውታል፡፡

ይህን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት ለኔታንያሁ ደውለው ነግረዋቸዋል፡፡ በመቀጠልም ስምምነቱን ለማፅናት ወደ ፓኪስታን ደውለው የሀገሪቱን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዠ አሲም ሙኒርን አግኝተው ተነጋግረዋል፡፡ መግለጫ ባወጡ በ15 ደቂቃ ውስጥ ደግሞ የአሜሪካ ጦር ጥቃቱን እንዲያቆም ትዕዛዝ ደረሰው። የኢራኑ አራቅጂ ሀገራቸው የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደምታከብርና የሆርሙዝ ሰርጥን ክፍት እንደምትያደርግ የገለጹት ከዚህ በኋላ ነው።

የፊታችን ጁምዐ በፓኪስታን ለሚካሄደው ድርድር ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄ ዲ ቫንስ፤ የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነርን አስከትለው ወደ ኢስላምአባድ ይጓዛሉ፡፡ በኢራን በኩል ማን እንደሚወከል እስካሁን ይፋ አልተደረገም፡፡ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ለስምምነት በሚቀርቡት ጉዳዮች ላይ አሁንም ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ በዚህም ጦርነቱ እንደገና ሊቀሰቀስ የሚችልበትን ዕድል ክፍት ሊያደርገው ይችላል የሚለውን ሥጋት የሚያነሱ ታዛቢዎች አሉ፡፡

(ይህ ዘገባ የተጠናቀረው አክሲዮስ፣ ሚድል ኢስት ዐይ፣ አልጀዚራ እና አሶሽዬጽ ፕረስን በምንጭነት በመጠቀም ነው)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular