በሚያንማር የወታደራዊው መንግሥት ኃይሎች በአራካን ግዛት ሲትዌ ከተማ በሚገኙ የፖሊስና የወታደራዊ ሻለቃዎች አቅራቢያ ያሉ ሁለት የሙስሊም መንደሮችን በሙሉ አውድመዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት፤ ወታደሮቹ መንደሮቹ ያወደሙት “ለፀጥታ አስጊ ናቸው” የሚል ሰበብ በማቅረብ ነው፡፡
ከአራት ቀናት በፊት የተጀመረው መኖሪያ መንደሮችን የማውደም ተግባር የተጀመረው በቁጥር 12 የፖሊስ ሻለቃ ዋና መሥሪያ ቤት አቅራቢያ የሚገኙትን ‘ታንዳውሊ’ እና ‘ኢማባሪ’ በመባል በሚጠሩ የሙስሊም መንደሮች መሆኑን የበርማ እና አካባቢው ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው በርማ ኒውስ ኢንተርናሽናል ድረ ገጽ ዘገባ ያመለክታል፡፡
አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለዜና ምንጩ፤ “ቤቶቹ ሲፈርሱ እያተመለከትን ነው፤ በድርጊቱ ላይ ሠራዊቱም ሆነ ፖሊስ እየተሳተፉበት ይገኛል” ማለታቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ በዚህ ውድመት ምክንያት ከከተማው ዳርቻ የሚገኙ በርካታ የሙስሊም ቤተሰቦች ተፈናቅለው ወደ ከተማው እምብርት በመግባት በተጨናነቁ ገዳማት ውስጥ ለመጠለል ተገደዋል፡፡ ይህም በዋና ከተማዋ ውስጥ ያለውን የተፈናቃዮች ቁጥር እንዲያሻቅብ አድርጓል። ነዋሪውም፦ “ጦርነቱ እየበረታ ሲመጣ ብዙ ሙስሊሞች ወደ ከተማው ገብተዋል፤ ከዚህ ቀደም በሠራዊቱ የተባረሩ በርካታ የአራካን ነዋሪዎችም ወደ ከተማው መጥተው በገዳሙ አቅራቢያ ተጠልለዋል” ሲሉ ይህን አረጋግጠዋል፡፡
ውድመቱ ቲንጂያን በመባል የሚጠራው የምያንማር አዲስ ዓመት ፌስቲቫል ከመከበሩ አስቀድሞ “የመከላከያ ቀጠና” ለመፍጠር የተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ዓላማውም የአራካን ጦር ተዋጊዎች ወታደራዊ ተቋማትን ጥቃት ለማድረስ መንደሮቹን እንደ መሸሸጊያ እንዳይጠቀሙባቸው ለመከላከል የሚል ነው። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በአቅራቢው የሚገኙ ሁሉም የሙስሊም መንደሮች በቀጣይ ይወድማሉ።
ከወደሙት መካከል ታንዳውሊ መንደር በተደጋጋሚ ውጊያ በሚካሄድበት ስትራቴጂያዊ ነው በሚባለው ሽዌሚንጋንግ አቅራቢያ ትገኛለች። ወታደራዊ ኃይሉ በአሁኑ ጊዜ የሲትዌ ነዋሪዎችን ከአራካን ጦር ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል እያሰረ መሆኑም ተነግሯል፡፡ ኃይሉ ከአራካን ጦር ጋር እንዲዋጉ እ.አ.አ ከ2025 ጀምሮ በሲትዌ ስር በሚገኙ 10 የሙስሊም መንደሮች ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች ወታደራዊ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። አሁን ባለው ውጊያ ላይ ወታደራዊ ኃይሉ እነዚህን የሰለጠኑ ነዋሪዎች ለውጊያ የተጠቀመባቸው ሲሆን፣ ይህም ለሞትና ለከፍተኛ የእርስ በእርስ መከዳዳት ምክንያት መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል። (ሚንበር ቲቪ)












