ዋና መቀመጫውን በባህሬን ያደረገውና በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የባንክ ዘርፎች ላይ የተሰማራው ኢንተርኮንቲነንታል ኢንቨስትመንት ባንክ ግሩፕ (iibGroup)፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአዲስ አበባ የውክልና ቢሮ መክፈት የሚያስችለውን ፍቃድ ማግኘቱን አስታውቋል።
አይአይቢ ግሩፕ ይህን ያሳወቀው በድረ ገጽ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 15 የውጭ ባንኮች የውክልና ቢሮዎች ቢኖሩም የማሻሻያ ደንቡ ከወጣ በኋላ ፈቃድ በማግኘት የመጀመሪያው መሆኑን ገለጿል፡፡ ማሻሻያው በውጭ ኢንቨስትመንት፣ በንግድ ማመቻቸት እና በፋይናንሺያል አገልግሎት ፈጠራ አዳዲስ እድሎችን እንደሚከፍት በመግለጫው አስፍሯል። ተቋሙ በጅቡቲ በኩል አይ ‘አይ ቢ ኢስት አፍሪካ’ በሚል ሥያሜ የሚንቀሳቀስ ሲሆን የአዲስ አበባ ቢሮው በኢትዮጵያና በጅቡቲ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ የንግድ ትስስር ለማጠናከር እንደሚሠራም አስታውቋል።
ቢሮው ከሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ግንኙነት መፍጠር፣ የገበያ ጥናቶችን ማካሄድ እና ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎቶችን ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች እንደ ድልድይ ሆኖ እንደሚያገለግል በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡ በአዲስ አበባ የቢሮው ዋና ተወካይ ዓይናለም አባቡ፤ “ዓላማችን በኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች እና በዓለም አቀፍ ገበያ መካከል ድልድይ መሆን ነው” ብለዋል።
እንደ ቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ያሉ ግዙፍ መሠረተ ልማቶችና በዙርያው ለሚገነቡ ልማቶች “የውጭ ኢንቨስትመንት ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ እንሠራለን” ሲሉም አክለዋል። የአይ አይ ቢ ግሩፕ ሊቀመንበር ሱሃይል ሡልጣን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ውስጥ ካሉ እጅግ አጓጊ የገበያ ዕድሎች መካከል አንዷ እንደሆነች ተናግረዋል፡፡
አይ አይ ቢ ግሩፕ በአሁኑ ወቅት በምሥራቅ አፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በምዕራብ አፍሪካ እና በካሪቢያን አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የባንክ፣ የኢንቨስትመንት፣ የዲጂታል መሰረተ ልማት እና የፋይናንስ ተደራሽነት አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል። ባንኩ የእስላማዊ እና መደበኛ የባንክ አገልግሎቶችን ጎን ለጎን የሚያቀርብ ተቋም ሲሆን፤ በምሥራቅ አፍሪካ ጅቡቲ የሚንቀሳቀሰው ሙሉ በሙሉ ሸሪዓን መሠረት ባደረገ አገልግሎት ነው። (ሚንበር ቲቪ)












