Homeዜናና ወቅታዊዜናበኢራን እና አሜሪካ የ45 ቀናት የተኩስ አቁም?

በኢራን እና አሜሪካ የ45 ቀናት የተኩስ አቁም?

  • በኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዓባስ አራቅጂ እና በትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና መካከል የጽሑፍ መልዕክቶች ልውውጥ ቀጥለዋል

አሜሪካ፣ ኢራን እና የቀጣናው አሸማጋዮች ጦርነቱን በዘላቂነት ሊያስቆም የሚችልና ለ45 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ውይይት እያካሄዱ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡ የመረጃው ምንጭ የአሜሪካው አክስዮስ፤ የአሜሪካ፣ የእስራኤል እና የቀጣናውን ምንጮች ነግረውኛል እንዳለው ከሆነ፤ ድርድሩ ቢቀጥልም በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውስጥ መጠነኛም ቢሆን “ስምምነት ላይ የመድረስ ዕድሉ ጠባብ ነው”። ነገር ግን ይህ የመጨረሻው ጥረት፣ በኢራን የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ሊሰነዘር የሚችለውን መጠነ ሰፊ ጥቃት እና በባሕረ ሰላጤው ሀገሮች የኃይል እና የውኃ ተቋማት ላይ ሊወሰድ የሚችለውን አጸፋዊ እርምጃ ጨምሮ ጦርነቱ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዳይሸጋገር ለመከላከል “እንደ ብቸኛ ዕድል” ተደርጎ ተወስዷል፡፡

ይህ የድርድር ሂደት የተሰማው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት የሰጡት ቀነ ገደብ ነገ ማክሰኞ መጋቢት 29 በአሜሪካ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 8 ሰዓት እንደሚያበቃ ዛቻ ከሰነዘሩ በኋላ ነው፡፡ ፕሬዝዳንቱ ስምምነት ካልተደረገ “ሁሉንም ነገር አፈነዳለሁ” ሲሉ ዝተዋል። ኢራን ቀደም ሲል በኩዌት፣ በባሕሬን እና በተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ የነዳጅ እና የውኃ ማጣሪያ ተቋማት ላይ ጥቃት የሰነዘረች ሲሆን፣ አሁንም የአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት ከቀጠለ “የበለጠ አስከፊ” ርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቃለች።

በሀገሮቹ መካከል የሚደረገው የድርድር ሂደቱ የሚመራው በፓኪስታን፣ ግብፅ እና ቱርክ አማካኝነት ነው፡፡ ሦስቱ ሀገሮች ከሚያደርጉት የሽምግልና ጥረት ባሻገር በኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዓባስ አራቅጂ እና በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ መካከል የጽሑፍ መልዕክቶች ልውውጥ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን እንደገለጹት፤ የትራምፕ አስተዳደር ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ለኢራን በርካታ ምክረ ሐሳቦችን ያቀረበ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ የኢራን ባለሥልጣናት የሚቀበሉት አልሆነም። የመጀመሪያው ምዕራፍ ለ45 ቀናት ሊቆይ የሚችል የተኩስ አቁም ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ጦርነቱን በቋሚነት ለማቆም የሚያስችል ድርድር ይካሄዳል፡፡ ለንግግሮቹ ተጨማሪ ጊዜ የሚያስፈልግ ከሆነ የተኩስ አቁሙ ሊራዘም ይችላል ተብሏል። ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ጦርነቱን በዘላቂነት ስለማቆም የሚደረግ ስምምነት ይሆናል። የኢራን ባለሥልጣናት ለአሸማጋዮች በወረቀት ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት በማስፈር አሜሪካ እና እስራኤል በፈለጉ ጊዜ ጥቃት ሊሰነዝሩባቸው የሚችሉበት እንደ ጋዛ ወይም ሊባኖስ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መገኘት አንፈልግም ሲሉ በግልጽ ነግረዋቸዋል፡፡

የአክስዮስ ዘገባ ይህን ቢልም የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጣሂር አንድራቢ፣ ፓኪስታን በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ እስራኤል እና በኢራን መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ምክረ ሐሳብ አቅርባለች የሚሉ ዘገባዎችን “ለማረጋገጥም ሆነ ለማስተባበል” ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ አንድራቢ ለዜና ምንጩ ሲናገሩ፦ “የ45 ቀናት የተኩስ አቁም የውሳኔ ሐሳብ ወይም ባለ 15 ነጥብ የሰነድ ልውውጥ ስለመኖሩ የሚገልጹ በርካታ ዘገባዎች አሉ፤ እኛ ግን በእነዚህ ነጠላና ግለሰባዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አስተያየት አንሰጥም፤ የእኛ ነጥብ የሰላም ሂደቱ ቀጥሏል የሚል ነው” ብለዋል።

በአንጻሩ አንድ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደገለጹት፤ ሀገራቸው በፓኪስታን በኩል የቀረበላትን የአስቸኳይ የተኩስ አቁም የውሳኔ ሐሳብ ተቀብላ እየመረመረችው መሆኑን አረጋግጠዋል። ሆኖም ግን ቴህራን የጊዜ ገደቦችን እንድትቀበልና ውሳኔ እንድታስተላልፍ የሚደረግባትን ተጽዕኖ እንደማትቀበልም አስታውቀዋል። እኒህ ባለሥልጣን ኢራን በጊዜያዊ የተኩስ አቁም ምትክ የሆርሙዝ ወሽመጥን “አትከፍትም” ያሉ ሲሆን፤ ቴህራን ዋሽንግተንን ለቋሚ የተኩስ አቁም “ዝግጁነት እንደሌላት አድርጋ እንደምትመለከታትም” ገልጸዋል። የኢራን አብዮታዊ ዘብ የባሕር ኃይልም እሑድ ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለው ሁኔታ በተለይም ለአሜሪካ እና ለእስራኤል በፍጹም ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት አይመለስም ብሏል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular