Homeዜናና ወቅታዊዜናየእስራኤል ሠፈራ እንዲቆም እና የወንጀል ተጠያቂነት እንዲሰፍን የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በተመድ ጉባኤ...

የእስራኤል ሠፈራ እንዲቆም እና የወንጀል ተጠያቂነት እንዲሰፍን የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በተመድ ጉባኤ በአብላጫ ድምጽ ጸደቀ

በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በተካሄደው 61ኛው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ላይ የቀረበው የእስራኤል ሠፈራ እንዲቆም እና የወንጀል ተጠያቂነት እንዲሰፍን የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በ34 ድጋፍ፣ በሦስት ተቃውሞ እና በዐሥር ድምጽ ተዓቅቦ ጸድቋል፡፡ በዚህ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ኢትዮጵያ በተቃውሞ ድምጽ ከሰጡ ሦስት ሀገሮች መካከል አንደኛዋ ሆናለች፡፡

ይህ የውሳኔ ሐሳብ በፍልስጤማውያን ንጹሐን ዜጎች ላይ የጥቃት፣ የማስፈራራት፣ ትንኮሳ ወይም የሽብር ተግባር የሚፈጽሙ ሰፋሪዎችን፣ የሰፋሪ ቡድኖችን እና አባላቶቻቸውን ማንነት የሚዘረዝር ሪፖርት በገለልተኛ ዓለም አቀፍ የምርመራ ኮሚሽን እንዲያዘጋጅ በድጋሚ የተጠየቀበት ነው፡፡ ሪፖርቱ ወራሪዋ ኃይል እስራኤል እና ሌሎች ሀገሮች ዓለም አቀፍ ሕግን በሚጥሱ ሰፋሪዎች ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የወሰዷቸውን ርምጃዎች እንዲያካትት ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ ይህ ሪፖርት ለምክር ቤቱ በ67ኛው መደበኛ ጉባኤ እንዲቀርብ የተጠየቀ ሲሆን፣ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ደግሞ በ64ኛው ጉባኤ ላይ የውሳኔውን አፈጻጸም እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የፍልስጤም ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ላይ ድምጽ ሰጥቷል፡፡ የውሳኔ ሐሳቡ በ42 ድጋፍ፣ በዜሮ ተቃውሞ እና በአምስት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን የውሳኔ ሐሳብ ከደገፉት ውስጥ ተካታለች፡፡

በዚህ ውሳኔ ሐሳብ ወራሪዋ ኃይል እስራኤል ምሥራቅ ቁድስን ጨምሮ በግዳጅ በተያዙ የፍልስጤም ግዛቶች ያደረገችውን ሕገ ወጥ ሠፈራ በአፋጣኝ እንዲያበቃ ጥሪ ቀርቧል። ለፍልስጤም የፖለቲካ ነፃነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንቅፋት የሆኑ ነገሮች በሙሉ እንዲወገዱ እና እንዲታረሙ የሚጠይቀው የውሳኔ ሐሳቡ፤ ሁሉም ሀገሮች እስራኤል ለምትፈጽማቸው ከባድ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰቶች ዕውቅና እንዳይሰጡ፣ እንዲሁም ምንም ዓይነት ድጋፍና ርዳታ እንዳያደርጉ ያሳስባል። በመጨረሻም ሀገሮች እነዚህን ጥሰቶች በሕጋዊ መንገድ ለማስቆም በጋራ እንዲሠሩ እና የፍልስጤም ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱ እንዲከበር አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦበታል፡፡

ጉባኤውን በተመለከተ መረጃ ያወጣው በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት፤ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል በመሆን በጉባኤው ወቅት መግባባትን በመፍጠር እና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ላይ “የሚታይ፣ ንቁ እና ገንቢ ሚና” ተጫውታለች ብሏል። በዚህ መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ መግለጫ በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ክቡር አምባሳደር ፀጋአብ ከበበው ማቅረባቸውን አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ሰላምን ለማስፈንና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እየተገበረች ያለውን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስረድታለች። ይህም ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር፣ እርቅን ለማውረድ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት እንደ ወሳኝ ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡(ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular