Homeዜናና ወቅታዊዜናበአሜሪካ የሚንቀሳቀሰው የሙስሊሞች ተሟጋች ቡድን “ሰብዓዊነት የጎደለው” ነው ያለው የትራምፕ ዛቻ ላይ...

በአሜሪካ የሚንቀሳቀሰው የሙስሊሞች ተሟጋች ቡድን “ሰብዓዊነት የጎደለው” ነው ያለው የትራምፕ ዛቻ ላይ ነቀፌታ ሠነዘረ

  • የፕሬዝዳንት ትራምፕን ንግግር ተከትሎ ነዳጅ ከፍተኛ ጭማሪ ሲያሳይ፣ የአክስዮን ገበያ ቀንሷል

በአሜሪካ የሚንቀሳቀሰው ዘ ካውንስል ኦን አሜሪካን ሪሌሽንስ (CAIR)፣ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ኢራንን ወደ ድንጋይ ዘመን እመልሳታለሁ” በማለት የሰነዘሩትን ማስጠንቀቂያ በጽኑ ነቅፏል። ቡድኑ ባወጣው መግለጫ የፕሬዝዳንቱ ንግግር “ፀረ ሙስሊም፣ ዘረኛ እና ሰብዓዊነትን የሚያሳጣ ነው” ብሎታል፡፡

ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ቀስቃሽ ንግግሮች በአሜሪካ በሚኖሩ ሙስሊም ማኅበረሰቦች ላይ የጥላቻ ጥቃቶችን እና የእስልምና ጥላቻን ሊያባብሱ እንደሚችሉ ስጋቱን በመግለጽም፤ አስተዳደሩ ከእንዲህ ዓይነት “አደገኛ ንግግሮች” እንዲቆጠብ አሳስቧል።

ዘ ካውንስል ኦን አሜሪካን ሪሌሽንስ፤ የትራምፕ አስተዳደር እስራኤል ሀገሪቱን “ያለ አሜሪካ ሕዝብ ፍላጎት ሕገ ወጥ ለሆነ የወረራ ጦርነት ውስጥ እንድትጎትተን ፈቅዶላታል” ሲል ወቀሳ ሰንዝሯል፡፡ ኮንግረሱ በሚቀጥለው ሣምንት ሥራ ሲጀምር የጦርነት ሥልጣን ውሳኔን እንዲያጸድቅ እና ለጦርነቱ የሚውል “ተጨማሪ በጀትን እንዲያስቆም” አሳስቧል። ቡድኑ የጠቀሰው ውሳኔ የአሜሪካ ኮንግረስ ፕሬዝዳንቱ ያለ ኮንግረሱ ፍቃድ ጦርነት የማወጅ ወይም ጦር የማዘዝ ሥልጣናቸውን ለመገደብ እ.ኤ.አ. በ1973 ያጸደቀው የፌዴራል ሕግ ነው። በተጨማሪም በመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴዝ ላይ በጦር ወንጀል በአፋጣኝ ምርመራ እንዲጀመር ጥሪ አቅርቧል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱ ከመጠናቀቁ በፊት በሚቀጥሉት ሁለት እና ሦስት ሣምንታት ውስጥ ኢራንን “ወደ ድንጋይ ዘመን ለመመለስ” ያነጣጠረ ከፍተኛ የቦምብ ድብደባ እንደሚቀጥል የገለጹት ትናንት ምሽት ባደረጉት ንግግር ነው፡፡ በዚሁ መግለጫ አሜሪካ በኢራን ላይ ወታደራዊ ርምጃ የወሰደችው በቀጠናው ያሉ አጋሮቿን ለመደገፍ መሆኑን ይፋ አድርገዋል። ይህ መግለጫ እስራኤል ዋሽንግተን በቴህራን ላይ ጥቃት እንድትሰነዝር ለረዥም ጊዜ ስታደርግ የነበረውን ጥረት የሚያመላክት ነው ተብሏል።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው አሜሪካ አሁን በኢነርጂ ዘርፍ ራሷን የቻለች መሆኗን ጠቅሰው፣ “ከመካከለኛው ምሥራቅ ምንም የምንፈልገው ነገር የለም፤ ዘይታቸውንም አንፈልግም፤ እዚያ የምንገኘው አጋሮቻችንን ለመርዳት ብቻ ነው” ብለዋል። በተጨማሪም በ32 ቀናት ውስጥ የተከናወነው ወታደራዊ ዘመቻ “ፈጣን እና ወሳኝ” ውጤት ማምጣቱን የገለጹት ትራምፕ፣ የጦርነቱ ዋና ዋና ስልታዊ ግቦች ወደ መጠናቀቅ መቃረባቸውን ገልጸዋል።

ትራምፕ ይህን የተናገሩት ኢራን ዩናይትድ ስቴትስን የተኩስ አቁም ጠይቃለች ካሉ ከጥቂት ሰዐታት በኋላ ነው። ነገር ግን እርሳቸው ጥያቄውን የሚቀበሉት የሆርሙዝ መተላለፊያን ከከፈተች ብቻ መሆኑን ገልጸው ነበር። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የትራምፕን ንግግር ወዲያውኑ አስተባብሏል። ቴህራን ከዋሽንግተን ጋር ምንም ዐይነት የቀጥታ ድርድር እያደረገች እንዳልሆነ በተደጋጋሚ መግለጿንም ቀጥላለች።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ምሽት አሜሪካ በኢራን ላይ የምታካሄደውን ወታደራዊ ጥቃት እንደምትቀጥል መናገራቸውን ተከትሎ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በአንድ በርሜል ከአምስት ዶላር በላይ ጭማሪ አሳይቷል። በዚሁ ሳቢያ የጃፓን፣ የቻይና እና የደቡብ ኮሪያ አክሲዮን ገበያዎች ቅናሽ አሳይተዋል። ኢራን ለአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት በሰጠችው የአጸፋ ምላሽ የሆርሙዝ ሰርጥን ከዘጋች በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚሠራጨው የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ውስጥ አንድ አምስተኛው መቋረጡ ይታወቃል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular